ምዕራፍ 1

በተራራማው በኤፍሬም አገር ከአርማቴም መሴፋ የሆነ ስሙ ሕልቃና የተባለ ኤፍሬማዊ ሰው ነበረ፤ እርሱም የኢያሬምኤል ልጅ የኢሊዮ ልጅ የቶሑ ልጅ የናሲብ ልጅ ነበረ።
2 ፤ ሁለትም ሚስቶች ነበሩት፤ የአንዲቱ ስም ሐና የሁለተኛይቱም ስም ፍናና ነበረ፤ ለፍናናም ልጆች ነበሩአት፥ ለሐና ግን ልጅ አልነበራትም።
3 ፤ ያም ሰው በሴሎ ይሰግድ ዘንድ ለሠራዊት ጌታም ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ከከተማው በየዓመቱ ይወጣ ነበር። የእግዚአብሔርም ካህናት ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በዚያ ነበሩ።
4 ፤ ሕልቃና የሚሠዋበት ቀን በደረሰ ጊዜም ለሚስቱ ለፍናና ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ሁሉ እድል ፈንታቸውን ሰጣቸው።
5 ፤ ሐናንም ይወድድ ነበርና ለሐና ሁለት እጥፍ እድል ፈንታ ሰጣት። እግዚአብሔር ግን ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበር።
6 ፤ እግዚአብሔርም ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበርና ጣውንትዋ ታስቆጣት ታበሳጫትም ነበር።
7 ፤ በየዓመቱም እንዲህ ባደረገ ጊዜ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር በምትወጣበት ጊዜ ታበሳጫት ነበር፤ ሐናም ታለቅስ ነበር፥ አንዳችም አትቀምስም ነበር።
8 ፤ ባልዋም ሕልቃና። ሐና ሆይ፥ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትቀምሺም? ለምንስ ልብሽ ያዝንብሻል? እኔስ ከአሥር ልጆች አልሻልልሽምን? አላት።
9 ፤ በሴሎ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሣች። ካህኑም ዔሊ በእግዚአብሔር መቅደስ መቃን አጠገብ በመንበሩ ላይ ተቀምጦ ነበር።
10 ፤ እርስዋም በልብዋ ትመረር ነበር፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸለየች፥ ጽኑ ልቅሶም አለቀሰች።
11 ፤ እርስዋም። አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፥ እኔንም ባትረሳ፥ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፥ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም ብላ ስእለት ተሳለች።
12 ፤ ጸሎትዋንም በእግዚአብሔር ፊት ባበዛች ጊዜ ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር።
13 ፤ ሐናም በልብዋ ትናገር ነበር፤ ድምፅዋም ሳይሰማ ከንፈርዋን ታንቀሳቅስ ነበር፤ ዔሊም እንደ ሰከረች ቈጠራት።
14 ፤ ዔሊም። ስካርሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አርቂው አላት።
15 ፤ ሐናም። ጌታዬ ሆይ፥ አይደለም፥ እኔስ ልብዋ ያዘነባት ሴት ነኝ፤ ጠጅና ሌላ የሚያሰክር ነገር አልጠጣሁም፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ነፍሴን አፈሰስሁ፤
16 ፤ ኀዘኔና ጭንቀቴ ስለ በዛ እስከ አሁን ድረስ ተናግሬአለሁና ባሪያህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቍጠረኝ ብላ መለሰችለት።
17 ፤ ዔሊም። በደኅና ሂጂ፥ የእስራኤልም አምላክ የለመንሽውን ልመና ይስጥሽ ብሎ መለሰላት።
18 ፤ እርስዋም። ባሪያህ በዓይንህ ፊት ሞገስ ላግኝ አለች። ሴቲቱም መንገድዋን ሄደች በላችም፥ ፊትዋም ከእንግዲህ ወዲያ አዘንተኛ መስሎ አልታየም።
19 ፤ ማልደው ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፥ ተመልሰውም ወደ አርማቴም ወደ ቤታቸው መጡ። ሕልቃናም ሚስቱን ሐናን አወቃት፤ እግዚአብሔርም አሰባት፤
20 ፤ የመፅነስዋም ወራት ካለፈ በኋላ ሐና ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርስዋም። ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ ስትል ስሙን ሳሙኤል ብላ ጠራችው።
21 ፤ ሰውዮውም ሕልቃና ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር የዓመቱን መሥዋዕትና ስእለቱን ለእግዚአብሔር ያቀርብ ዘንድ ወጣ።
22 ፤ ሐና ግን አልወጣችም፥ ባልዋንም። ሕፃኑ ጡት እስኪተው ድረስ እቀመጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ፥ በዚያም ለዘላለም ይሆን ዘንድ አመጣዋለሁ አለችው።
23 ፤ ባልዋም ሕልቃና። በዓይንሽ ደስ ያሰኘሽን አድርጊ፥ ጡትም እስኪተው ድረስ ተቀመጪ፤ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን ያጽና አላት። ሴቲቱም ልጅዋን እያጠባች ጡት እስኪተው ድረስ በቤትዋ ተቀመጠች።
24 ፤ ጡትም በተወ ጊዜ ከእርስዋ ጋር እርሱንና አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፥ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት፥ አንድ አቁማዳ የወይን ጠጅ ይዛ ወደ ሴሎ ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጣችው፤ ሕፃኑም ገና ታናሽ ነበረ።
25 ፤ ወይፈኑንም አረዱ፥ ሕፃኑንም ወደ ዔሊ አመጡት።
26 ፤ እርስዋም አለች። ጌታዬ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታ ሆይ፥ ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ በዚህ በአንተ ዘንድ ቆማ የነበረች ሴት እኔ ነኝ።
27 ፤ ሰለዚህ ሕፃን ጸለይሁ፤
28 ፤ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ልመናዬን ሰጥቶኛል፤ እኔም ደግሞ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል።