ምዕራፍ 5

ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ወሰዱ፤ ከአቤንኤዘርም ወደ አዛጦን ይዘውት መጡ።
2 ፤ ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው ወደ ዳጎን ቤት አገቡት፥ በዳጎንም አጠገብ አኖሩት።
3 ፤ በነጋውም የአዛጦን ሰዎች ማለዱ፥ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር፤ ዳጎንንም አንሥተው ወደ ስፍራው መለሱት።
4 ፤ በነጋውም ማለዱ፥ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር፤ የዳጎንም ራስ እጆቹም ተቈርጠው በመድረኩ ላይ ወድቀው ነበር፤ የዳጎንም ደረት ብቻውን ቀርቶ ነበር።
5 ፤ ስለዚህም የዳጎን ካህናት ወደ ዳጎንም ቤት የሚገቡት ሁሉ በአዛጦን ያለውን የዳጎንን መድረክ እስከ ዛሬ ድረስ አይረግጡም።
6 ፤ የእግዚአብሔርም እጅ በአዛጦን ሰዎች ላይ ከበደች፥ አጠፋቸውም፥ አዛጦንንና ድንበራቸውንም በእባጭ መታቸው።
7 ፤ የአዛጦንም ሰዎች እንዲህ እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ። እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክራለችና የእስራኤል አምላክ ታቦት ከእኛ ዘንድ አይቀመጥ አሉ።
8 ፤ ልከውም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ወደ እነርሱ ሰበሰቡና። በእስራኤል አምላክ ታቦት ምን እናድርግ? አሉ፤ እነርሱም። የእስራኤል አምላክ ታቦት ወደ ጌት ይዙር ብለው መለሱ። የእስራኤልንም አምላክ ታቦት ወደዚያ ተሸከሙት።
9 ፤ ከተሸከሙትም በኋላ የእግዚአብሔር እጅ በታላቅ ድንጋጤ በከተማይቱ ላይ ሆነች፤ ከታናሹም እስከ ታላቁ ድረስ የከተማይቱን ሰዎች መታ፥ እባጭም መጣባቸው።
10 ፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት ወደ አስቀሎና ሰደዱት። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ አስቀሎና በመጣ ጊዜ አስቀሎናውያን። እኛንና ሕዝባችንን ሊገድሉ የእስራኤልን አምላክ ታቦት አመጡብን ብለው ጮኹ።
11 ፤ በከተማይቱ ሁሉ የሞት ድንጋጤ ነበርና፥ የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ እጅግ ከብዳ ነበረችና ልከው የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ሰብስበው። የእስራኤልን አምላክ ታቦት ስደዱ፥ እኛንና ሕዝባችንን እንዳይገድል ወደ ስፍራው ይመለስ አሉ።
12 ፤ ያልሞቱትም ሰዎች በእባጭ ተመቱ፤ የከተማይቱም ዋይታ እስከ ሰማይ ወጣ።