ምዕራፍ 27

ዳዊትም በልቡ። አንድ ቀን በሳኦል እጅ እጠፋለሁ፤ ወደ ፍልስጥኤማውያንም ምድር ከመሸሽ በቀር የሚሻለኝ የለም፤ ሳኦልም በእስራኤል አውራጃ ሁሉ እኔን መሻት ይተዋል፥ እንዲሁም ከእጁ እድናለሁ አለ።
2 ፤ ዳዊትም ከእርሱም ጋር የነበሩት ስድስቱ መቶ ሰዎች ተነሥተው ወደ ጌት ንጉሥ ወደ አሜህ ልጅ ወደ አንኩስ አለፉ።
3 ፤ ዳዊትና ሰዎቹም እያንዳንዳቸው ከነ ቤተ ሰቡ ከአንኩስ ጋር በጌት ውስጥ ተቀመጡ፤ ከዳዊትም ጋር ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት አቢግያ ሁለቱ ሚስቶቹ ነበሩ።
4 ፤ ሳኦልም ዳዊት ወደ ጌት እንደ ኰበለለ ሰማ፤ ከዚያም በኋላ ደግሞ አልፈለገውም።
5 ፤ ዳዊትም አንኩስን። በዓይንህ ፊት ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ በዚህ አገር በአንዲቱ ከተማ የምቀመጥበት ስፍራ ስጠኝ፤ ስለ ምን እኔ ባሪያህ ከአንተ ጋር በንጉሥ ከተማ እቀመጣለሁ? አለው።
6 ፤ በዚያም ቀን አንኩስ ጺቅላግን ሰጠው፤ ስለዚህም ጺቅላግ እስከ ዛሬ ድረስ ለይሁዳ ነገሥታት ሆነች።
7 ፤ ዳዊትም በፍልስጥኤማውያን አገር የተቀመጠበት የዘመን ቍጥር አንድ ዓመት ከአራት ወር ነበረ።
8 ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ወጥተው በጌሹራውያንና በጌርዛውያን በአማሌቃውያንም ላይ ዘመቱ፤ እነዚህም እስከ ሱር እስከ ግብጽ ምድር ድረስ ባለው አገር ድሮውኑ ተቀምጠው ነበር።
9 ፤ ዳዊትም ምድሪቱን መታ፤ ወንድ ሆነ ሴትም ሆነ ማንንም በሕይወት አልተወም፤ በጎችንና ላሞችን አህያዎችንና ግመሎችን ልብስንም ማረከ፥ ተመልሶም ወደ አንኩስ መጣ።
10 ፤ አንኩስም። ዛሬ በማን ላይ ዘመታችሁ? አለ፤ ዳዊትም። በይሁዳ ደቡብ፥ በይረሕምኤላውያንም ደቡብ፥ በቄናውያንም ደቡብ ላይ ዘመትን አለ።
11 ፤ ዳዊት እንዲህ አደረገ በፍልስጥኤማውያንም አገር በሚቀመጥበት ዘመን ሁሉ ልማዱ ይህ ነበረ ብለው እንዳይናገሩብን ብሎ ዳዊት ወደ ጌት ያመጣቸው ዘንድ ወንድም ሆነ ሴትም ሆነ ማንንም በሕይወት አልተወም።
12 ፤ አንኩስም። በሕዝቡ በእስራኤል ዘንድ እጅግ የተጠላ ሆኖአል፤ ስለዚህም ለዘላለም ባሪያ ይሆነኛል ብሎ ዳዊትን አመነው።