ምዕራፍ 31

ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወደቁ።
2 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ።
3 ፤ ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ ቀስተኞችም አገኙት፤ እርሱም ከቀስተኞቹ የተነሣ እጅግ ተጨነቀ።
4 ፤ ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን። እነዚህ ቈላፋን መጥተው እንዳይወጉኝና እንዳይሳለቁብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ።
5 ፤ ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ በሰይፉ ላይ ወደቀ፥ ከእርሱም ጋር ሞተ።
6 ፤ በዚያም ቀን ሳኦል ሦስቱም ልጆቹ ጋሻ ጃግሬውም ሰዎቹም ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ።
7 ፤ በሸለቆውም ማዶና በዮርዳኖስ ማዶ የነበሩ እስራኤላውያን የእስራኤል ሰዎች እንደ ሸሹ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቹን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው።
8 ፤ በማግሥቱም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው።
9 ፤ የሳኦልንም ራስ ቈረጠው የጦር ዕቃውን ገፍፈው ለጣዖታቱ መቅደስ ለሕዝቡም የምስራች ይሰጥ ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ሁሉ ሰደዱ።
10 ፤ የጦር ዕቃውንም በአስታሮት መቅደስ ውስጥ አኖሩት፤ ሬሳውንም በቤትሳን ቅጥር ላይ አንጠለጠሉት።
11 ፤ ፍልስጥኤማውያንም በሳኦል ላይ ያደረጉትን የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች በሰሙ ጊዜ፥
12 ፤ ጀግኖች ሰዎች ሁሉ ተነሥተው ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ፥ የሳኦልንም ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ከቤትሳን ቅጥር ላይ አወረዱ፤ ወደ ኢያቢስም መጡ፥ በዚያም አቃጠሉት።
13 ፤ አጥንታቸውንም ወሰዱ በኢያቢስም ባለው በአጣጡ ዛፍ በታች ቀበሩት፥ ሰባት ቀንም ጾሙ።