ምዕራፍ 11

እንዲህም ሆነ፤ ከአንድ ወር በኋላ አሞናዊው ናዖስ ወጣ፥ በኢያቢስ ገለዓድም ሰፈረ፤ የኢያቢስም ሰዎች ሁሉ። ቃል ኪዳን አድርግልን፥ እኛም እንገዛልሃለን አሉት።
2 ፤ አሞናዊውም ናዖስ። ቀኝ ዓይናችሁን ሁሉ በማውጣት ቃል ኪዳን አደርግላችኋለሁ፤ በእስራኤልም ሁሉ ላይ ስድብ አደረጋለሁ አላቸው።
3 ፤ የኢያቢስም ሽማግሌዎች። ወደ እስራኤል አገር ሁሉ መልክተኞችን እንድንልክ ሰባት ቀን ቆይልን፤ ከዚያም በኋላ የሚያድነን ባይኖር ወደ አንተ እንመጣለን አሉት።
4 ፤ መልክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው ይህን ነገር በሕዝቡ ጆሮ ተናገሩ፤ ሕዝቡም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ።
5 ፤ እነሆም፥ ሳኦል በሬዎቹን ተከትሎ ከእርሻው መጣ፤ ሳኦልም። ሕዝቡ የሚያለቅስ ምን ሆኖ ነው? አለ። የኢያቢስንም ሰዎች ነገር ነገሩት።
6 ፤ ይህንም ነገር በሰማው ጊዜ በሳኦል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደ፥ ቍጣውም እጅግ ነደደ።
7 ፤ ጥምዱንም በሬዎች ወስዶ ቈራረጣቸው፥ ወደ እስራኤልም ዳርቻ ሁሉ በመልክተኞቹ እጅ ሰደደና። ሳኦልንና ሳሙኤልን ተከትሎ የማይወጣ ሁሉ፥ በበሬዎቹ እንዲሁ ይደረግ አለ። ድንጋጤም በሕዝቡ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደቀ፥ እንደ አንድ ሰውም ሆነው ወጡ።
8 ፤ በቤዜቅም ቈጠራቸው፤ የእስራኤልም ልጆች ሦስት መቶ ሺህ፥ የይሁዳም ሰዎች ሠላሳ ሺህ ነበሩ።
9 ፤ የመጡትንም መልክተኞች። የኢያቢስ ገለዓድን ሰዎች። ነገ ፀሐይ በተኮሰ ጊዜ ማዳን ይሆንላችኋል በሉአቸው አሉአቸው። መልክተኞችም መጥተው ለኢያቢስ ሰዎች ነገሩ፤ ደስም አላቸው።
10 ፤ የአያቢስም ሰዎች። ነገ እንወጣላችኋለን፥ ደስ የሚያሰኛችሁንም አድርጉብን አሉ።
11 ፤ በነጋውም ሳኦል ሕዝቡን በሦስት ወገን አደረጋቸው፤ ወገግም ባለ ጊዜ ወደ ሰፈሩ መካከል ገቡ፥ ቀትርም እስኪሆን ድረስ አሞናውያንን መቱ፤ የቀሩትም ተበተኑ፥ ሁለትም በአንድ ላይ ሆነው አልቀሩላቸውም።
12 ፤ ሕዝቡም ሳሙኤልን። ሳኦል አይንገሥብን ያሉ እነማናቸው? አውጡአቸውና እንግደላቸው አሉት።
13 ፤ ሳኦልም። ዛሬ እግዚአብሔር ለእስራኤል ማዳን አድርጎአልና ዛሬ አንድ ሰው አይሞትም አለ።
14 ፤ ሳሙኤልም ሕዝቡን። ኑ፥ ወደ ጌልገላ እንሂድ፥ በዚያም መንግሥቱን እናድስ አላቸው።
15 ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ጌልገላ ሄዱ፥ በዚያም ሳኦልን በእግዚአብሔር ፊት በጌልገላ አነገሡት፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት የደኅንነት መሥዋዕት አቀረቡ፤ በዚያም ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ታላቅ ደስታ አደረጉ።