ምዕራፍ 4

እስራኤልም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሊዋጋ ወጡ፥ በአቤንኤዘር አጠገብ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያን በአፌቅ ሰፈሩ።
2 ፤ ፍልስጥኤማውያንም በእስራኤል ላይ ተሰለፉ፤ ሰልፉም በተመደበ ጊዜ እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ፊት ተመቱ፤ ጦርነት በተደረገበትም ስፍራ ከእስራኤል አራት ሺህ የሚያህሉ ሰዎችን ገደሉ።
3 ፤ ሕዝቡም ወደ ሰፈር በመጡ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎች። ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ፊት ስለ ምን መታን? በመካከላችን እንዲሄዱ፥ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ አሉ።
4 ፤ ሕዝቡም ወደ ሴሎ ላኩ፥ በኪሩቤልም ላይ የሚቀመጠውን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከዚያ አመጡ፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ።
5 ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፥ ምድሪቱም አስተጋባች።
6 ፤ ፍልስጥኤማውያንም የእልልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ። በዕብራውያን ሰፈር ያለው ይህ ታላቅ የእልልታ ድምፅ ምንድር ነው? አሉ። የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ሰፈሩ እንደገባ አስተዋሉ።
7 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው። እግዚአብሔር ወደ ሰፈር መጥቶአል አሉ። ደግሞም እንዲህ አሉ። ወዮልን፤ ከዚህ አስቀድሞ እንዲህ ያለ ነገር አልሆነም።
8 ፤ ወዮልን፤ ከእነዚህ ከኃያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነዚህ አማልክት ግብጻውያንን በምድረ በዳ በልዩ በልዩ መቅሠፍት የመቱ ናቸው።
9 ፤ እናንተ ፍልስጥኤማውያን ሆይ፥ አይዞአችሁ፥ ጎብዙ፤ እናንተ ባሪያዎች እንዳደረጋችኋቸው ዕብራውያን ባሪያዎች እንዳያደርጉአችሁ ጎብዙ፥ ተዋጉ።
10 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ተዋጉ፤ እስራኤልም ተመቱ፥ ሁሉም እያንዳንዱ ወደ ድንኳናቸው ሸሹ፤ እጅግም ታላቅ ግድያ ሆነ፥ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኞች ወደቁ።
11 ፤ የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከች፥ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ።
12 ፤ በዚያም ቀን አንድ የብንያም ሰው ከሰልፍ እየበረረ ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ ወደ ሴሎ መጣ።
13 ፤ በመጣም ጊዜ ዔሊ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ልቡ ተናውጦ ነበርና በመንገድ ዳር በወንበሩ ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር፤ ሰውዮውም ወደ ከተማይቱ ገብቶ ባወራ ጊዜ ከተማይቱ ሁሉ ተጭዋጭዋኸች።
14 ፤ ዔሊም የጩኸቱን ድምፅ በሰማ ጊዜ። ይህ ጫጫታ ምንድር ነው? አለ። ሰውዮውም ፈጥኖ መጣና ለዔሊ ነገረው።
15 ፤ ዔሊም የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ነበረ፤ ዓይኖቹም ማየት እስኪሳናቸው ድረስ ፈዝዘው ነበር።
16 ፤ ሰውዮውም ዔሊን። ከሰልፍ የመጣሁ እኔ ነኝ፥ ዛሬም ከሰልፍ ኮበለልሁ አለ። እርሱም። ልጄ ሆይ፥ ነገሩሳ እንዴት ሆነ? አለው።
17 ፤ ወሬኛውም መልሶ። እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ ታላቅ ግድያ ሆኖአል፥ ሁለቱም ልጆችህ አፍኒንና ፊንሐስ ሞተዋል፤ የእግዚአብሔርም ታቦት ተማርካለች አለ።
18 ፤ ሰውዮውም ስለ እግዚአብሔር ታቦት በተናገረ ጊዜ ዔሊ በበሩ አጠገብ ካለው ከወንበሩ ወደቀ፤ እርሱ ሸምግሎ ደንግዞም ነበርና አንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እርሱም በእስራኤል ላይ አርባ ዓመት ፈራጅ ነበረ።
19 ፤ ምራቱም የፊንሐስ ሚስት አርግዛ ልትወልድ ተቃርባ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ታቦት እንደ ተማረከች፥ አማትዋና ባልዋም እንደ ሞቱ በሰማች ጊዜ ምጥ ደርሶባት ነበርና ተንበርክካ ወለደች።
20 ፤ ወደሞትም በቀረበች ጊዜ በዙሪያዋ ያሉት ሴቶች። ወንድ ልጅ ወልደሻልና አትፍሪ አሉአት። እርስዋ ግን አልመለሰችላቸውም፥ በልብዋም አላኖረችውም።
21 ፤ እርስዋም የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከች ስለአማትዋና ስለ ባልዋም። ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የሕፃኑን ስም። ኢካቦድ ብላ ጠራችው።
22 ፤ እርስዋም። የእግዚአብሔር ታቦት ተማርካለችና ክብር ከእስራኤል ለቀቀ አለች።