ምዕራፍ 19

ሳኦልም ለልጁ ለዮናታንና ለባሪያዎቹ ሁሉ ዳዊትን ይገድሉ ዘንድ ነገራቸው። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድድ ነበር።
2 ፤ ዮናታንም። አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ፈልጎአል፤ አሁን እንግዲህ ለነገው ተጠንቅቀህ ተሸሸግ፥ በስውርም ተቀመጥ፤
3 ፤ እኔም እወጣለሁ አንተም ባለህበት እርሻ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፥ ስለ አንተም ከአባቴ ጋር እነጋገራለሁ፤ የሆነውንም አይቼ እነግርሃለሁ ብሎ ለዳዊት ነገረው።
4 ፤ ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል። እርሱ አልበደለህምና። ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፤
5 ፤ ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊውን ገደለ፥ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ሁሉ ታላቅ መድኃኒት አደረገ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ፤ በከንቱ ዳዊትን በመግደልህ ስለምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ? ብሎ ስለ ዳዊት መልካም ተናገረ።
6 ፤ ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፤ ሳኦልም። ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም ብሎ ማለ።
7 ፤ ዮናታንም ዳዊትን ጠርቶ ይህን ነገር ሁሉ ነገረው፤ ዮናታንም ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፥ እንደ ቀድሞውም በፊቱ ነበረ።
8 ፤ ደግሞም ጦርነት ሆነ፤ ዳዊትም ወጥቶ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ ታላቅ ግዳይም ገደላቸው፥ ከፊቱም ሸሹ።
9 ፤ ሳኦልም ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው። ዳዊትም በእጁ በገና ይመታ ነበር።
10 ፤ ሳኦልም ዳዊትን ከግንብ ጋር ያጣብቀው ዘንድ ጦሩን ወረወረ፤ ዳዊትም ከሳኦል ፊት ዘወር አለ፥ ጦሩም በግንቡ ውስጥ ተተከለ፤ በዚያም ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ።
11 ፤ ሳኦልም ዳዊትን ጠብቀው በነጋው እንዲገድሉት መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ቤት ላከ፤ ሚስቱም ሜልኮል። በዚህች ሌሊት ነፍስህን ካላዳንህ ነገ ትገደላለህ ብላ ነገረችው።
12 ፤ ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አወረደችው፤ ሄደም፥ ሸሽቶም አመለጠ።
13 ፤ ሜልኮልም ተራፊምን ወስዳ በአልጋ ላይ አኖረችው፥ በራስጌውም ጕንጕን የፍየል ጠጉር አደረገች፥ በልብስም ከደነችው።
14 ፤ ሳኦልም ዳዊትን እንዲያመጡት መልእክተኞችን ላከ፥ እርስዋም። ታምሞአል አለቻቸው።
15 ፤ ሳኦልም። እገድለው ዘንድ ዳዊትን ከነ አልጋው አምጡልኝ ብሎ መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ሰደደ።
16 ፤ መልእክተኞቹም በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ተራፊሙን በአልጋው ላይ አገኙ፥ በራስጌውም ጕንጕን የፍየል ጠጉር ነበረ።
17 ፤ ሳኦልም ሜልኮልን። ስለ ምን እንዲህ አድርገሽ አታለልሽኝ? ጠላቴን አስኰበለልሽው አላት። ሜልኮልም ለሳኦል። እርሱ። አውጥተሽ ስደጂኝ፥ አለዚያም እገድልሻለሁ አለኝ ብላ መለሰችለት።
18 ፤ ዳዊትም ሸሽቶ አመለጠ፥ ወደ አርማቴምም ወደ ሳሙኤል መጣ፥ ሳኦልም ያደረገበትን ሁሉ ነገረው፤ እርሱና ሳሙኤልም ሄዱ በነዋትዘራማም ተቀመጡ።
19 ፤ ሳኦልም። ዳዊት፥ እነሆ፥ በአርማቴም አገር በነዋትዘራማ ተቀምጦአል የሚል ወሬ ሰማ።
20 ፤ ሳኦልም ዳዊትን ያመጡት ዘንድ መልእክተኞችን ሰደደ፤ የነቢያት ጉባኤ ትንቢት ሲናገሩ፥ ሳሙኤልም አለቃቸው ሆኖ ሲቆም ባዩ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል መልእክተኞች ላይ ወረደ፥ እነርሱም ትንቢት ይናገሩ ጀምር።
21 ፤ ሳኦልም ያንን በሰማ ጊዜ ሌሎች መልእክተኞችን ሰደደ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። ሳኦልም እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ መልእክተኞችን ሰደደ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ።
22 ፤ የሳኦልም ቍጣ ነደደ፥ እርሱም ደግሞ ወደ አርማቴም መጣ፥ በሤኩም ወዳለው ወደ ታላቁ የውኃ ጕድጓድ ደረሰ። ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው? ብሎ ጠየቀ፤ አንድ ሰውም። እነሆ፥ በአርማቴም አገር በነዋትዘራማ ናቸው አለው።
23 ፤ ወደ አርማቴምም አገር ወደ ነዋትዘራማ ሄደ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ደግሞ ወረደ፥ እርሱም ሄደ፥ ወደ አርማቴምም አገር ወደ ነዋትዘራማ እስኪመጣ ድረስ ትንቢት ይናገር ነበር።
24 ፤ ልብሱንም አወለቀ፥ በሳሙኤልም ፊት ትንቢት ተናገረ፥ ራቁቱንም ወድቆ በዚያ ቀን ሁሉ በዚያም ሌሊት ሁሉ ተጋደመ። ስለዚህ። ሳኦል ደግሞ ከነቢያት መካከል ነውን? ይባባሉ ነበር።