ምዕራፍ 24

እንዲህም ሆነ፤ ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ከተመለሰ በኋላ። እነሆ፥ ዳዊት በዓይንጋዲ ምድረ በዳ አለ የሚል ወሬ ደረሰለት።
2 ፤ ሳኦልም ከእስራኤል ሁሉ የተመረጡትን ሦስት ሺህ ሰዎች ወሰደ፥ ዳዊትንና ሰዎቹንም ለመፈለግ የበረሀ ፍየሎች ወደ ነበሩባቸው ዓለቶች ሄደ።
3 ፤ በመንገድም አጠገብ ወዳሉት የበጎች ማደሪያዎች መጣ፥ በዚያም ዋሻ ነበረ፤ ሳኦልም ወገቡን ይሞክር ዘንድ ከዚያ ገባ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ከዋሻው በውስጠኛው ቦታ ተቀምጠው ነበር።
4 ፤ የዳዊትም ሰዎች። እነሆ፥ ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ በዓይንህም ደስ የሚያሰኝህን ታደርግበታለህ ብሎ እግዚአብሔር የነገረህ ቀን፥ እነሆ፥ ዛሬ ነው አሉት። ዳዊትም ተነሥቶ የሳኦልን መጎናጸፊያ ዘርፍ በቀስታ ቈረጠ።
5 ፤ ከዚያም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የሳኦልን የልብሱን ዘርፍ ስለቈረጠ የዳዊት ልብ በኀዘን ተመታ።
6 ፤ ሰዎቹንም። እግዚአብሔር የቀባው ነውና እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር አደርግ ዘንድ እጄንም እጥልበት ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው አላቸው።
7 ፤ ዳዊትም በዚህ ቃል ሰዎቹን ከለከላቸው፥ በሳኦልም ላይ ይነሡ ዘንድ አልተዋቸውም፤ ሳኦልም ከዋሻው ተነሥቶ መንገዱን ሄደ።
8 ፤ ከእርሱም በኋላ ዳዊት ደግሞ ተነሣ፥ ከዋሻውም ወጣ፥ ከሳኦልም በኋላ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ብሎ ጮኸ፤ ሳኦልም ወደ ኋላው ተመለከተ፥ ዳዊትም ወደ ምድር ተጐንብሶ እጅ ነሣ።
9 ፤ ዳዊትም ሳኦልን አለው። እነሆ፥ ዳዊት ክፉ ነገር ይሻብሃል የሚሉህን ሰዎች ቃል ለምን ትሰማለህ?
10 ፤ እነሆ፥ ዛሬ በዋሻው ውስጥ እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ እንደ ሰጠህ ዓይንህ አይታለች፤ አንተንም እንድገድልህ ሰዎች ተናገሩኝ፤ እኔ ግን። በእግዚአብሔር የተቀባ ነውና እጄን በጌታዬ ላይ አልዘረጋም ብዬ ራራሁልህ።
11 ፤ ደግሞም፥ አባቴ ሆይ፥ የልብስህ ዘርፍ በእጄ እንዳለ ተመልክተህ እወቅ፤ የልብስህንም ዘርፍ በቈረጥሁ ጊዜ አልገደልሁህም፤ ስለዚህም በእጄ ክፋትና በደል እንደሌለ፥ አንተም ነፍሴን ልትወስድ ምንም ብታሳድደኝ እንዳልበደልሁህ ተመልክተህ እወቅ።
12 ፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ፥ እግዚአብሔርም አንተን ይበቀልልኝ፤ እጄ ግን በአንተ ላይ አትሆንም።
13 ፤ በጥንት ምሳሌ። ከኃጢአተኞች ኀጢአት ይወጣል እንደ ተባለ፤ እጄ ግን በአንተ ላይ አትሆንም።
14 ፤ የእስራኤል ንጉሥ ማንን ለማሳደድ መጥቶአል? አንተስ ማንን ታሳድዳለህ? የሞተ ውሻን ወይስ ቁንጫን ታሳድዳለህን?
15 ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር ዳኛ ይሁን፥ በእኔና በአንተም መካከል ይፍረድ፥ አይቶም ይምዋገትልኝ፥ ከእጅህም ያድነኝ።
16 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት ይህን ቃል ለሳኦል መናገር በፈጸመ ጊዜ፥ ሳኦል። ልጄ ሆይ ዳዊት፥ ይህ ድምፅህ ነውን? አለ፤ ሳኦልም ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ።
17 ፤ ዳዊትን አለው። እኔ ክፉ በመለስሁልህ ፋንታ በጎ መልሰህልኛልና አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ።
18 ፤ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለ አልገደልኸኝምና ለእኔ መልካም እንዳደረግህልኝ አንተ ዛሬ አሳየኸኝ።
19 ፤ ጠላቱን አግኝቶ በመልካም መንገድ ሸኝቶ የሚሰድድ ማን ነው? ስለዚህ ለእኔ ስላደረግኸው ቸርነት እግዚአብሔር ይመልስልህ።
20 ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ አንተ በእርግጥ ንጉሥ እንድትሆን የእስራኤልም መንግሥት በእጅህ እንድትጸና እኔ አውቃለሁ።
21 ፤ አሁን እንግዲህ ከእኔ በኋላ ዘሬን እንዳትቈርጥ ከአባቴም ቤት ስሜን እንዳታጠፋው በእግዚአብሔር ማልልኝ።
22 ፤ ዳዊትም ለሳኦል ማለለት፤ ሳኦልም ወደ ቤቱ ሄደ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ አምባው ወጡ።