ምዕራፍ 16

እግዚአብሔርም ሳሙኤልን። በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? በቀንድህ ዘይቱን ሞልተህ ሂድ፤ በልጆቹ መካከል ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ አለው።
2 ፤ ሳሙኤልም። እንዴት እሄዳለሁ? ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል አለ። እግዚአብሔርም። አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፥ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ በል።
3 ፤ እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፥ የምታደርገውንም አስታውቅሃለሁ፤ የምነግርህንም ቅባልኝ አለው።
4 ፤ ሳሙኤልም እግዚአብሔር የተናገረውን አደረገ፥ ወደ ቤተ ልሔምም መጣ። የአገሩም ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡና። የመጣኸው ለደኅንነት ነውን? አሉት።
5 ፤ እርሱም። ለደኅንነት ነው፤ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ፤ ቅዱሳን ሁኑ፥ ከእኔም ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ አለ። እሴይንና ልጆቹንም ቀደሳቸው፥ ወደ መሥዋዕቱም ጠራቸው።
6 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በመጡ ጊዜ ወደ ኤልያብ ተመልክቶ። በእውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው አለ።
7 ፤ እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን። ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው።
8 ፤ እሴይም አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት አሳለፈው፤ እርሱም። ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ።
9 ፤ እሴይም ሣማን አሳለፈው፤ እርሱም። ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ።
10 ፤ እሴይም ከልጆቹ ሰባቱን በሳሙኤል ፊት አሳለፋቸው። ሳሙኤልም እሴይን። እግዚአብሔር እነዚህን አልመረጠም አለው።
11 ፤ ሳሙኤልም እሴይን። የቀረ ሌላ ልጅ አለህን? አለው። እርሱም። ታናሹ ገና ቀርቶአል፤ እነሆም፥ በጎችን ይጠብቃል አለ። ሳሙኤልም እሴይን። እርሱ እስኪመጣ ድረስ አንረፍቅምና ልከህ አስመጣው አለው።
12 ፤ ልኮም አስመጣው፤ እርሱም ቀይ፥ ዓይኑም የተዋበ፥ መልኩም ያማረ ነበረ። እግዚአብሔርም። ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው አለ።
13 ፤ ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ።
14 ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፥ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አሠቃየው።
15 ፤ የሳኦልም ባሪያዎች። እነሆ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሠቃይሃል፤
16 ፤ በገና መልካም አድርጎ የሚመታ ሰው ይሹ ዘንድ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን ባሪያዎቹን ይዘዝ፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ክፉ መንፈስ በሆነብህ ጊዜ በእጁ ሲመታ አንተ ደኅና ትሆናለህ አሉት።
17 ፤ ሳኦልም ባሪያዎቹን። መልካም አድርጎ በገና መምታት የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ አላቸው።
18 ፤ ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ። እነሆ፥ መልካም አድርጎ በገና የሚመታ የቤተ ልሔማዊውን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፤ እርሱም ጽኑዕ ኃያል ነው፥ በነገርም ብልህ፥ መልኩም ያማረ ነው፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው አለ።
19 ፤ ሳኦልም ወደ እሴይ መልክተኞች ልኮ። ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ አለ።
20 ፤ እሴይም እንጀራና የወይን ጠጅ አቁማዳ የተጫነ አህያ የፍየልም ጠቦት ወስዶ በልጁ በዳዋት እጅ ወደ ሳኦል ላከ።
21 ፤ ዳዊትም ወደ ሳኦል መጣ፥ በፊቱም ቆመ፤ እጅግም ወደደው፥ ለእርሱም ጋሻ ጃግሬው ሆነ።
22 ፤ ሳኦልም ወደ እሴይ። በዓይኔ ሞገስ አግኝቶአልና ዳዊት በፊቴ፥ እባክህ፥ ይቁም ብሎ ላከ።
23 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፤ ሳኦልንም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር፥ ክፉ መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር።