ምዕራፍ 28

እንዲህም ሆነ፤ በዚያ ወራት ከእስራኤል ጋር ይዋጉ ዘንድ ፍልስጥኤማውያን ጭፍሮቻቸውን ለሰልፍ ሰበሰቡ፤ አንኩስም ዳዊትን። አንተና ሰዎችህ ከእኔ ጋር ወደ ሰልፍ እንድትወጡ በእርግጥ እወቅ አለው።
2 ፤ ዳዊትም አንኩስን። አሁን ባሪያህ የሚያደርገውን ታያለህ አለው። አንኩስም ዳዊትን። እንግዲህ በዘመኑ ሁሉ ራሴን ጠባቂ አደርግሃለሁ አለው።
3 ፤ ሳሙኤል ግን ሞቶ ነበር፥ እስራኤልም ሁሉ አልቅሰውለት ነበር፥ በከተማውም በአርማቴም ቀብረውት ነበር። ሳኦልም መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር አጥፍቶ ነበር።
4 ፤ ፍልስጥኤማውያንም ተሰብስበው መጡ በሱነምም ሰፈሩ፤ ሳኦልም እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ በጊልቦዓም ሰፈሩ።
5 ፤ ሳኦልም የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ባየ ጊዜ ፈራ፥ ልቡም እጅግ ተንቀጠቀጠ።
6 ፤ ሳኦልም እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም በሕልም ወይም በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም።
7 ፤ ሳኦልም ባሪያዎቹን። ወደ እርስዋ ሄጄ እጠይቅ ዘንድ መናፍስትን የምትጠራ ሴት ፈልጉልኝ አላቸው፤ ባሪያዎቹም። እነሆ፥ መናፍስትን የምትጠራ አንዲት ሴት በዓይንዶር አለች አሉት።
8 ፤ ሳኦልም መልኩን ለውጦ ሌላ ልብስም ለብሶ ሄደ፥ ሁለትም ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ፥ በሌሊትም ወደ ሴቲቱ መጡ። እርሱም። እባክሽ፥ በመናፍስት አምዋርቺልኝ፥ የምልሽንም አስነሽልኝ አላት።
9 ፤ ሴቲቱም። እነሆ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር እንዳጠፋ ሳኦል ያደረገውን ታውቃለህ፤ ስለ ምን እኔን ለማስገደል ወጥመድ ለነፍሴ ታደርጋለህ? አለችው።
10 ፤ ሳኦልም። ሕያው እግዚአብሔርን! በዚህ ነገር ቅጣት አያገኝሽም ብሎ በእግዚአብሔር ማለላት።
11 ፤ ሴቲቱም። ማንን ላስነሣልህ? አለች፤ እርሱም። ሳሙኤልን አስነሽልኝ አለ።
12 ፤ ሴቲቱም ሳሙኤልን ባየች ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኸች፤ ሴቲቱም ሳኦልን። አንተ ሳኦል ስትሆን ለምን አታለልኸኝ? ብላ ተናገረችው።
13 ፤ ንጉሡም። አትፍሪ፤ ያየሽው ምንድር ነው? አላት። ሴቲቱም ሳኦልን። አማልክት ከምድር ሲወጡ አየሁ አለችው።
14 ፤ እርሱም። መልኩ ምን ዓይነት ነው? አላት። እርስዋም። ሽማግሌ ሰው ወጣ፤ መጐናጸፊያም ተጐናጽፎአል አለች። ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ሆነ አወቀ፥ በፊቱም ተጐነበሰ፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣ።
15 ፤ ሳሙኤልም ሳኦልን። ለምን አወክኸኝ? ለምንስ አስነሣኸኝ? አለው። ሳኦልም መልሶ። ፍልስጥኤማውያን ይወጉኛልና እጅግ ተጨንቄአለሁ፥ እግዚአብሔርም ከእኔ ርቆአል፤ በነቢያት ወይም በሕልም አልመለሰልኝም፤ ስለዚህም የማደርገውን ታስታውቀኝ ዘንድ ጠራሁህ አለው።
16 ፤ ሳሙኤልም አለ። እግዚአብሔር ከራቀህ ጠላትም ከሆነህ ለምን ትጠይቀኛለህ?
17 ፤ እግዚአብሔርም በቃሌ እንደ ተናገረ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም መንግሥትህን ከእጅህ ነጥቆ ለጎረቤትህ ለዳዊት ሰጥቶታል።
18 ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና፥ በአማሌቅም ላይ ታላቅ የሆነ ቍጣውን አላደረግህምና ስለዚህ ዛሬ እግዚአብሔር ይህን ነገር አድርጎብሃል።
19 ፤ እግዚአብሔርም እስራኤልን ከአንተ ጋር በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል፤ ነገም አንተና ልጆችህ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ጭፍራ ደግሞ በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል።
20 ፤ ሳኦልም በዚያን ጊዜ በቁመቱ ሙሉ በምድር ላይ ወደቀ፥ ከሳሙኤልም ቃል የተነሣ እጅግ ፈራ። በዚያም ቀን ሁሉ በዚያም ሌሊት ሁሉ እንጀራ አልበላምና ኃይል አልቀረለትም።
21 ፤ ሴቲቱም ወደ ሳኦል መጣች፥ እጅግም ደንግጦ እንደ ነበረ አይታ። እነሆ፥ እኔ ባሪያህ ቃልህን ሰማሁ፥ ነፍሴንም በእጄ ጣልሁ፥ የነገርኸኝንም ቃል ሰማሁ።
22 ፤ አሁን እንግዲህ አንተ ደግሞ የባሪያህን ቃል እንድትሰማ እለምንሃለሁ፥ በፊትህም ቍራሽ እንጀራ ላኑርልህ፤ በመንገድም ስትሄድ ትበረታ ዘንድ ብላ አለችው።
23 ፤ እርሱ ግን። አልበላም ብሎ እንቢ አለ፤ ነገር ግን ባሪያዎቹና ሴቲቱ አስገደዱት፥ ቃላቸውንም ሰማ፤ ከምድርም ተነሥቶ በአልጋ ላይ ተቀመጠ።
24 ፤ ለሴቲቱም ማለፊያ እንቦሳ ነበራት፤ ፈጥና አረደችው፤ ዱቄቱንም ወስዳ ለወሰችው፥ ቂጣም እንጀራ አድርጋ ጋገረችው።
25 ፤ በሳኦልና በባሪያዎቹም ፊት አቀረበችው፤ በልተውም ተነሡ፥ በዚያም ሌሊት ሄዱ።