ምዕራፍ 11

ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው።
2 የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ስማ፥ ለይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ተናገር፥
3 -
4 እንደዚህም በላቸው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከግብጽ አገር ከብረት ምድጃ ባወጣኋቸው ቀን ለአባቶቻችሁ ያዘዝሁትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃል የማይሰማ ሰው ርጉም ይሁን፤ አልሁም። ቃሌን ስሙ፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።
5 ይህም ዛሬ እንደ ሆነ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻችሁ የማልሁትን መሐላ አጸና ዘንድ ነው። እኔም። አቤቱ፥ አሜን ብዬ መለስሁለት።
6 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ይህችን ቃል ሁሉ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ተናገር፥ እንዲህም በል። የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ስሙ አድርጉትም።
7 አባቶቻችሁን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በማለዳ ተነሥቼ እያስጠነቀቅሁ። ቃሌን ስሙ በማለት አስጠንቅቄአቸው ነበር።
8 እነርሱ ሁሉ ግን በክፉ ልባቸው እልከኝነት ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ ስለዚህ ያዘዝኋቸውን እነርሱም ያላደረጉትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ሁሉ አመጣሁባቸው።
9 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። በይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ዘንድ አድማ ተገኝቶአል።
10 ቃሌንም ይሰሙ ዘንድ እንቢ ወዳሉ ወደ አባቶቻቸው ኃጢአት ተመለሱ፥ ያመልኩአቸውም ዘንድ እንግዶችን አማልክት ተከተሉ፤ የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት ከአባቶቻቸው ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አፈረሱ።
11 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሊያመልጡት የማይችሉትን ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ፥ ወደ እኔም ይጮኻሉ፤ እኔም አልሰማቸውም።
12 በይሁዳም ከተሞችና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሄደው ወደሚያጥኑላቸው አማልክት ይጮኻሉ፤ ነገር ግን በመከራቸው ጊዜ ከቶ አያድኑአቸውም።
13 ይሁዳ ሆይ፥ አማልክትህ እንደ ከተሞችህ ቍጥር እንዲሁ ናቸው፤ እንደ ኢየሩሳሌምም መንገዶች ቍጥር ለነውረኛ ነገር መሠዊያ፥ እርሱም ለበኣል ታጥኑበት ዘንድ መሠዊያ፥ አድርጋችኋል።
14 አንተም ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ከመከራቸው የተነሣ ወደ እኔ በጮኹ ጊዜ አልሰማቸውምና ስለ እነርሱም ጩኸትና ልመና አታድርግ።
15 ወዳጄ በቤቴ ውስጥ ምን አላት? ስእለት ወይም የተቀደሰ ሥጋ ክፋትሽን ከአንቺ ያስወግዳልን? ወይስ በእነዚህ ታመልጫለሽን?
16 እግዚአብሔር ስምሽን።በመልካም ፍሬ የተዋበች የለመለመች የወይራ ዛፍ ብሎ ጠራው፤ በጽኑ ዐውሎ ነፋስ ጩኸት እሳትን አነደደባት፥ ቅርንጫፎችዋም ተሰብረዋል።
17 ለበኣልም በማጠናቸው ያስቈጡኝ ዘንድ ለራሳቸው ስለ ሠሩአት ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ ቤት ክፋት የተከለሽ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ክፉን ነገር ተናግሮብሻል።
18 እግዚአብሔርም አስታወቀኝ እኔም አወቅሁ፤ ሥራቸውንም ገለጥህልኝ።
19 እኔም ለመታረድ እንደሚነዳ እንደ የዋህ በግ ጠቦት ሆንሁ፤ እነርሱም። ዛፉን ከፍሬው ጋር እንቍረጥ፥ ስሙም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይታሰብ ከሕያዋን ምድር እናጥፋው ብለው ምክርን እንዳሰቡብኝ አላወቅሁም ነበር።
20 ኵላሊትንና ልብን የምትፈትን በቅንም የምትፈርድ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ ክርክሬን ገልጬልሃለሁና በእነርሱ ላይ የሚሆን በቀልህን ለይ።
21 ስለዚህም። በእጃችን እንዳትሞት በእግዚአብሔር ስም ትንቢት አትናገር ብለው ነፍስህን ስለሚሹ ስለ ዓናቶት ሰዎች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።እነሆ፥ እቀጣቸዋለሁ፤
22 ጎበዛዝቶቻቸው በሰይፍ ይሞታሉ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም በራብ ይሞታሉ፤ በምጐበኛቸውም ዓመት በዓናቶት ሰዎች ላይ ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁና ማንም ከእነርሱ የሚቀር የለም።
23