ምዕራፍ 50

እግዚአብሔር ስለ ከለዳውያን ምድር ስለ ባቢሎን በነቢዩ በኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው።
2 በአሕዛብ መካከል ተናገሩ አውሩም፥ ዓላማውንም አንሡ፤ አውሩ፥ አትደብቁ። ባቢሎን ተወሰደች፥ ቤል አፈረ፥ ሜሮዳክ ደነገጠ፤ ምስሎችዋ አፈሩ፥ ጣዖታትዋ ደነገጡ በሉ።
3 ሕዝብ ከሰሜን ወጥቶባታል ምድርዋንም ባድማ ያደርጋል፥ የሚቀመጥባትም አይገኝም፤ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ሸሽተው ሄደዋል።
4 በዚያም ወራት በዚያም ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ሆነው ይመጣሉ፥ እያለቀሱም መንገዳቸውን ይሄዳሉ፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ይፈልጋሉ።
5 ፊታቸውንም ወደዚያ አቅንተው። ኑ፥ ከቶ በማይረሳ በዘላለም ቃል ኪዳን ወደ እግዚአብሔር ተጠጉ ብለው ስለ ጽዮን መንገድ ይጠይቃሉ።
6 ሕዝቤ የጠፉ በጎች ሆነዋል፤ እረኞቻቸው አሳቱአቸው፥ በተራሮችም ላይ የተቅበዘበዙ አደረጉአቸው፤ ከተራራ ወደ ኮረብታ አለፉ፥ በረታቸውንም ረሱ።
7 ያገኙአቸው ሁሉ በሉአቸው፥ ጠላቶቻቸውም። በጽድቅ ማደሪያ በእግዚአብሔር ላይ፥ በአባቶቻቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ስለ ሠሩ እኛ አልበደልንም አሉ።
8 ከባቢሎን መካከል ሽሹ፥ ከከለዳውያንም ድር ውጡ፥ በመንጎችም ፊት እንደ አውራ ፍየሎች ሁኑ።
9 እነሆ፥ ከሰሜን ምድር የታላላቅ አሕዛብን ጉባኤ አስነሣለሁ በባቢሎንም ላይ አመጣቸዋለሁ፤ በእርስዋም ላይ ይሰለፋሉ፥ ከዚያም ትወሰዳለች፤ ፍላጾቻቸውም ባዶውን እንደማይመለስ እንደ ብልህ ጀግና ፍላጻ ናቸው።
10 የከላውዴዎንም ምድር ትበዘበዛለች፥ የሚበዘብዙአትም ሁሉ ይጠግባሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
11 ርስቴን የምትበዘብዙ እናንተ ሆይ፥ ደስ ብሎአችኋልና፥ ሐሤትንም አድርጋችኋልና፥ በመስክ ላይም እንዳለች ጊደር ሆናችሁ ተቀናጥታችኋልና፥ እንደ ብርቱዎችም ፈረሶች አሽካክታችኋልና፥
12 እናታችሁ እጅግ ታፍራለች፥ የወለደቻችሁም ትጐሰቍላለች፤ እነሆ፥ በአሕዛብ መካከል ኋለኛይቱ ትሆናለች፤ ምድረ በዳና ደረቅ ምድር በረሀም ትሆናለች።
13 ከእግዚአብሔር ቍጣ የተነሣ ባድማ ትሆናለች እንጂ ሰው አይቀመጥባትም፤ በባቢሎንም በኩል የሚያልፍ ሁሉ ይደነቃል በመጣባትም መቅሠፍት ሁሉ ያፍዋጫል።
14 እናንተ ቀስትን የምትገትሩ ሰዎች ሁሉ፥ በባቢሎን ላይ በዙሪያዋ ተሰለፉ፤ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርታለችና ወርውሩባት ፍላጾችንም አትንፈጉ።
15 የእግዚአብሔር በቀል ነውና በዙሪያዋ ጩኹባት፤ እጅዋን ሰጠች፤ ግንቦችዋ ወደቁ ቅጥሮችዋም ፈረሱ፤ እርስዋን ተበቀሉ እንደ ሠራችውም ሥሩባት።
16 ዘሪውንና በመከር ጊዜ ማጭድ የሚይዘውን ከባቢሎን አጥፉ፤ ከሚያስጨንቅ ሰይፍ ፊት እያንዳንዱ ወደ ወገኑ ይመለሳል እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሸሻል።
17 እስራኤል የባዘነ በግ ነው፤ አንበሶች አሳደዱት፤ መጀመሪያ የአሦር ንጉሥ በላው፥ በመጨረሻም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አጥንቱን ቈረጠመው።
18 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአሦርን ንጉሥ እንደ ቀጣሁ እንዲሁ፥ እነሆ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ምድሩን እቀጣለሁ።
19 እስራኤልንም ወደ ማሰማርያው እመልሳለሁ፥ በቀርሜሎስና በባሳንም ላይ ይሰማራል፥ ሰውነቱም በኤፍሬም ተራራና በገለዓድ ላይ ትጠግባለች።
20 እነዚህን ያስቀረኋቸውን ይቅር እላቸዋለሁና በዚያን ወራት በዚያም ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የእስራኤል በደል የይሁዳም ኃጢአት ይፈለጋል ምንም አይገኝም።
21 በምራታይም ምድር ላይ በፋቁድም በሚኖሩት ላይ ውጣ፤ ግደላቸው ፈጽመህም አጥፋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እንዳዘዝሁህም ሁሉ አድርግ።
22 የሰልፍና የታላቅ ጥፋት ውካታ በምድር ላይ አለ።
23 የምድር ሁሉ መዶሻ እንዴት ደቀቀ እንዴትስ ተሰበረ! ባቢሎንስ በአሕዛብ መካከል እንዴት ባድማ ሆነች!
24 ባቢሎን ሆይ፥ አጥምጄብሻለሁ አንቺም ሳታውቂ ተይዘሻል፤ ከእግዚአብሔር ጋር ስለ ተዋጋሽ ተገኝተሻል ተይዘሽማል።
25 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በከለዳውያን ምድር ይሠራ ዘንድ ሥራ አለውና እግዚአብሔር ዕቃ ቤቱን ከፍቶ የቍጣውን ዕቃ ጦር አውጥቶአል።
26 ከየበኩሉ በእርስዋ ላይ ውጡ፥ ጎተራዎችዋንም ክፈቱ፤ እንደ ክምርም አድርጓት ፈጽማችሁም አጥፉአት፥ አንዳችም አታስቀሩላት።
27 ወይፈኖችዋን ሁሉ እረዱ፥ ወደ መታረድም ይውረዱ፤ ቀናቸው፥ የመጐብኘታቸው ጊዜ፥ ደርሶአልና ወዮላቸው!
28 የአምላካችንን የእግዚአብሔርን በቀል የመቅደሱንም በቀል በጽዮን ይነግሩ ዘንድ ሸሽተው ከባቢሎን አገር ያመለጡት ሰዎች ድምፅ ተሰምቶአል።
29 ቀስትን የሚገትሩትን ቀስተኞችን ሁሉ በባቢሎን ላይ ጥሩአቸው፤ በዙሪያዋ ስፈሩባት አንድም አያምልጥ፤ በእስራኤል ቅዱስ ላይ በእግዚአብሔር ላይ ኰርታለችና እንደ ሥራዋ መጠን መልሱላት፥ እንዳደረገችም ሁሉ አድርጉባት።
30 ስለዚህ ጐበዛዝትዋ በአደባባይዋ ላይ ይወድቃሉ፥ በዚያም ቀን ሰልፈኞችዋ ሁሉ ይጠፋሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
31 ትዕቢተኛው ሆይ፥ የመጐብኘትህ ጊዜ፥ ቀንህ ደርሶአልና እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
32 ትዕቢተኛው ተሰናክሎ ይወድቃል የሚያነሣውም የለም፤ በከተሞቹም ውስጥ እሳት አነድዳለሁ፥ በዙሪያውም ያለውን ሁሉ ትበላለች።
33 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ተገፍተዋል፥ የማረኳቸውም ሁሉ በኃይል ይይዙአቸዋል፥ ይለቅቁአቸውም ዘንድ እንቢ ብለዋል።
34 ተቤዢአቸው ብርቱ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ ምድርንም ያሳርፍ ዘንድ በባቢሎንም የሚኖሩትን ያውክ ዘንድ ሙግታቸውን ፈጽም ይምዋገታል።
35 ሰይፍ በከለዳውያንና በባቢሎን በሚኖሩ ላይ፥ በአለቆችዋና በጥበበኞችዋ ላይ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር።
36 ሰይፍ በሚጓደዱት ላይ አለ ሰነፎችም ይሆናሉ፥ ሰይፍም በኃያላኖችዋ ላይ አለ እነርሱም ይደነግጣሉ።
37 ሰይፍ በፈረሶቻቸውና በሰረገሎቻቸው ላይ በመካከልዋም ባሉት በልዩ በልዩ ሕዝብ ሁሉ ላይ አለ፥ እነርሱም እንደ ሴቶች ይሆናሉ፤ ሰይፍም በመዝገብዋ ላይ አለ ለብዝበዛም ይሆናል።
38 እርስዋ የተቀረጹ ምስሎች ምድር ናት፥ እነርሱም በጣዖታት ይመካሉና ድርቅ በውኆችዋ ላይ ይሆናል እነርሱም ይደርቃሉ።
39 ስለዚህ የምድረ በዳ አራዊት ከተኵላዎች ጋር ይቀመጡባታል፥ ሰጐኖችም ይቀመጡባታል፤ ሰውም ከዚያ ወዲያ ለዘላለም አይቀመጥባትም፥ እስከ ልጅ ልጅም ድረስ የሚኖርባት የለም።
40 ሰዶምንና ገሞራን በአጠገባቸውም የነበሩትን ከተምች እግዚአብሔር እንደ ገለበጣቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እንዲሁ ሰው በዚያ አይቀመጥም የሰውም ልጅ አይኖርባትም።
41 እነሆ፥ ሕዝብ ከሰሜን ይመጣል ታላቅ ሕዝብና ብዙ ነገሥታትም ከምድር ዳርቻ ይነሣሉ።
42 ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፤ ጨካኞች ናቸው ምሕረትም አያደርጉም፤ ድምፃቸው እንደ ባሕር ይተምማል በፈረሶችም ላይ ይቀመጣሉ፤ የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ፥ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ።
43 የባቢሎን ንጉሥ ወሬአቸውን ሰምቶአል፥ እጁም ደክማለች፥ ጭንቀትም ይዞታል፥ ምጥ ወላድ ሴትን እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞታል።
44 እነሆ፥ ከእርስዋ ዘንድ በቶሎ አባርራቸዋለሁና በጠነከረው አምባ ላይ ከዮርዳኖስ ትዕቢት ውስጥ እንደ አንበሳ ይወጣል፤ የተመረጠውንም በእርስዋ ላይ እሾመዋለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ወይስ ለእኔ ጊዜ የሚወስን ማን ነው? ወይስ ፊቴን የሚቃወም እረኛ ማን ነው?
45 ስለዚህ እግዚአብሔር በባቢሎን ላይ የመከረባትን ምክር፥ በከለዳውያንም ምድር ላይ ያሰባትን አሳብ ስሙ፤ በእውነት የመንጋ ትናንሾች ይጎተታሉ፤ በእውነት ማደሪያቸውን ባድማ ያደርግባቸዋል።
46 ከባቢሎን መያዝ ድምፅ የተነሣ ምድር ተናወጠች፥ ጩኸትም በአሕዛብ መካከል ዘንድ ተሰማ።