ምዕራፍ 8

በዚያን ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የይሁዳን ነገሥታት አጥንትና የመኳንንቶቹን አጥንት፥ የካህናቱን አጥንትና የነቢያቱን አጥንት፥ የኢየሩሳሌምንም ሰዎች አጥንት ከመቃብራቸው ያወጣሉ።
2 በወደዱአቸውና ባመለኩአቸው፥ በተከተሉአቸውና በፈለጉአቸው፥ በሰገዱላቸውም በፀሐይና በጨረቃ በሰማይም ሠራዊት ሁሉ ፊት ይዘረጉአቸዋል፤ አያከማቹአቸውም አይቀብሩአቸውምም፥ በምድርም ፊት ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ።
3 እኔም ባሳደድኋቸው ስፍራ ሁሉ የቀሩ፥ ከዚህች ክፉ ወገን የተረፉ ቅሬታዎች ሁሉ፥ ከሕይወት ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ።
4 እንዲህም ትላቸዋለሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የወደቁ አይነሡምን? የሳተስ አይመለስምን?
5 እንግዲህ ይህ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ዘወትር ስለ ምን ወደ ኋላው ይመለሳል? ተንኰልን ይዞአል ሊመለስም እንቢ ብሎአል።
6 አደመጥሁ ሰማሁም፤ ቅንን ነገር አልተናገሩም፤ ማናቸውንም። ምን አድርጌአለሁ? ብሎ ከክፋቱ ንስሐ የገባ የለም፤ ወደ ሰልፍም እንደሚሮጥ ፈረስ እያንዳንዱ በየመንገዱ ይሄዳል።
7 ሽመላ በሰማይ ጊዜዋን አውቃለች፤ ዋኖስና ጨረባ ዋልያም የመምጣታቸውን ጊዜ ይጠብቃሉ፤ ሕዝቤ ግን የእግዚአብሔርን ፍርድ አላወቁም።
8 እናንተስ። ጥበበኞች ነን የእግዚአብሔርም ሕግ ከእኛ ጋር ነው እንዴት ትላላችሁ? እነሆ፥ የጸሐፊ ብርዕ ሐሰተኛ ነው በሐሰትም አድርጎአል።
9 ጥበበኞች አፍረዋል ደንግጠውማል ተማርከውማል፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ጥለዋል፤ ምን ዓይነት ጥበብ አላቸው?
10 ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ስስትን ያስባሉና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉ በተንኰል ያደርጋሉና ስለዚህ ሚስቶቻቸውን ለሌሎች፥ እርሻቸውንም ለሚወርሱባቸው እሰጣለሁ።
11 የሕዝቤንም ሴት ልጅ ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን። ስለም ሰላም ይላሉ።
12 አስጸያፊ ነገርን ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፥ እፍረትንም አላወቁም፤ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፤ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር
13 ፈጽሜ አጠፋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በወይን ላይ ፍሬ፥ በበለስ ዛፍ ላይ በለስ አይሆንም፥ ቅጠልም ይረግፋል፤ የሚያልፉባቸውንም ሰጠኋቸው።
14 ዝም ብለን ለም እንቀመጣለን? እግዚአብሔርን ስለ በደልን አምላካችን እግዚአብሔር አጥፍቶናልና፥ የሐሞትንም ውኃ አጠጥቶናልና ተሰብስባችሁ ወደ ተመሸጉ ከተሞች እንግባ በዚያም እንጥፋ።
15 ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፥ መልካምም አልተገኘም፤ መጠገንን በተስፋ ተጠባበቅን፥ እነሆም፥ ድንጋጤ ሆነ።
16 የፈረሰኞቹ ድምጽ ከዳን ተሰማ፤ ከአርበኞች ፈረሶች ማሽካካት የተነሣ ምድር ሁሉ ተንቀጠቀጠች፤ መጡም ምድሪቱንና በእርስዋም ያለውን ሁሉ፥ ከተማይቱንና የተቀመጡባትንም በሉ።
17 እነሆ፥ አስማት የማይከለክላቸውን እባቦችንና እፉኝቶችን እሰድድባችኋለሁ፤ እነርሱም ይነድፉአችኋል።
18 ኅዘኔ የማይጽናና ነው፥ ልቤም በውስጤ ደክሞአል።
19 እነሆ። እግዚአብሔር በጽዮን የለምን? ወይስ ንጉሥዋ በእርስዋ ዘንድ የለምን? የሚል የወገኔ ሴት ልጅ ጩኸት ድምፅ ከሩቅ አገር ተሰማ። በተቀረጹ ምስሎቻቸውና በባዕድ ከንቱነትስ ያስቈጡኝ ስለ ምንድር ነው?
20 መከሩ አልፎአል፥ በጋው ሄዶአል፥ እኛም አልዳንነም።
21 በሕዝቤ ሴት ልጅ ስብራት እኔ ተሰብሬአለሁ ጠKWreማለሁ፤ አድናቆትም ይዞኛል።
22 በገለዓድ የሚቀባ መድኃኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም የለምን? የወገኔ ሴት ልጅ ፈውስ ስለ ምን አልሆነም?