ምዕራፍ 12

አቤቱ፥ ከአንተ ጋር በተምዋገትሁ ጊዜ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ነገር ግን ከአንተ ጋር ስለ ፍርድ ልናገር። የኃጢአተኞች መንገድ ስለምን ይቃናል? በደልንስ ለሚያደርጉ ሁሉ ስለምን ደኅንነት ይሆናል?
2 ተክለሃቸዋል፤ ሥር ሰድደዋል፤ አድገዋል አፍርተውማል፤ በአፋቸው አንተ ቅርብ ነህ፥ ከልባቸው ግን ሩቅ ነህ።
3 አንተ ግን፥ አቤቱ፥ አውቀኸኛል፤ አይተኸኛል፥ ልቤንም በፊትህ ፈትነሃል፤ እንደ በጎች ለመታረድ ጐትተህ ለያቸው፥ ለመታረድም ቀን አዘጋጃቸው።
4 ምድሪቱ የምታለቅሰው፥ የአገሩ ሣርስ ሁሉ የሚደርቀው እስከ መቸ ነው? የተቀመጡባት ሰዎች። ፍጻሜያችንን አያይም ብለዋልና ስለ ክፋታቸው እንስሶችና ወፎች ጠፍተዋል።
5 ከእግረኞች ጋር በሮጥህ ጊዜ እነርሱ ቢያደክሙህ፥ ከፈረሶች ጋር መታገል እንዴት ትችላለህ? በሰላምም ምድር ታምነህ ብትቀመጥ፥ በዮርዳኖስ ትዕቢት እንዴት ታደርጋለህ?
6 ወንድሞችህና የአባትህ ቤት እነርሱ ጭምር አታልለውሃልና፥ በኋላህም ጮኸዋልና፤ በመልካምም ቢናገሩህም አትታመናቸው።
7 ቤቴን ትቼአለሁ ርስቴንም ጥያለሁ፥ ነፍሴም የምትወድዳትን በጠላቶችዋ እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ።
8 ርስቴ በዱር እንዳለ አንበሳ ሆናብኛለች፤ ድምፅዋን አንሥታብኛለች፤ ስለዚህ ጠልቻታለሁ።
9 ርስቴ እንደ ዝንጕርጕር አሞራ ሆነችብኝን? አሞሮችስ በዙሪያዋና በላይዋ ሆነዋልን? ሂዱ፥ የምድር አራዊትን ሁሉ ሰብስቡ፥ ይበሉም ዘንድ አምጡአቸው።
10 ብዙ እረኞች የወይኑን ቦታዬን አጥፍተዋል፥ እድል ፈንታዬንም ረግጠዋል፤ የአምሮቴን እድል ፈንታ ምድረ በዳ አድርገውታል።
11 ባድማ አድርገውታል፥ ፈርሶም ወደ እኔ ያለቅሳል፤ ምድር ሁሉ ባድማ ሆናለች በልቡም የሚያስባት የለም።
12 በወናዎች ኮረብቶች ሁሉ ላይ በዝባዦች መጥተዋል፥ የእግዚአብሔር ሰይፍ ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይበላልና፤ ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም።
13 ስንዴን ዘሩ እሾህንም አጨዱ፤ ደከሙ፥ ምንም አልረባቸውም፤ ስለ እግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ከፍሬያችሁ ታፍራላችሁ።
14 እግዚአብሔር ለሕዝቤ ለእስራኤል ያወረስሁትን ርስት ለሚነኩት ክፉዎች ጐረቤቶች ሁሉ እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ከምድራቸው እነቅላቸዋለሁ፥ የይሁዳንም ቤት ከመካከላቸው እነቅለዋለሁ።
15 ከነቀልኋቸውም በኋላ መልሼ እምራቸዋለሁ፥ እያንዳንዱንም ወደ ርስቱ እያንዳንዱንም ወደ ምድሩ እመልሳለሁ።
16 በበኣል ይምሉ ዘንድ ሕዝቤን እንዳስተማሩ በስሜ። ሕያው እግዚአብሔርን! ብለው ይምሉ ዘንድ የሕዝቤን መንገድ በትጋት ቢማሩ፥ በዚያን ጊዜ በሕዝቤ መካከል ይመሠረታሉ።
17 ባይሰሙኝ ግን ያንን ሕዝብ ፈጽሜ እነቅለዋለሁ አጠፋውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።