ምዕራፍ 27

በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ።
2 እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል። እስራትና ቀንበር ሥራ በአንገትህም ላይ አድርግ፤
3 ወደ ይሁዳ ንጉሥም ወደ ሴዴቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡት መልእክተኞች እጅ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ ወደ ሞዓብም ንጉሥ ወደ አሞንም ልጆች ንጉሥ ወደ ጢሮስም ንጉሥ ወደ ሲዶናም ንጉሥ ላካቸው።
4 ለጌቶቻቸውም እንዲነግሩ እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለጌቶቻችሁ እንዲህ በሉ።
5 ምድሪቱን በምድርም ፊት ላይ ያሉትን ሰዎችንና እንስሶችን በታላቅ ኃይሌና በተዘረጋችው ክንዴ ፈጥሬአለሁ፤ ለዓይኔም መልካም ለሆነው እሰጣታለሁ።
6 አሁንም እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለባሪያዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ፤ ይገዙለትም ዘንድ የምድረ በዳ አራዊትን ደግሞ ሰጥቼዋለሁ።
7 የገዛ ራሱም ምድር ጊዜ እስኪመጣ ድረስ አሕዛብ ሁሉ ለእርሱና ለልጅ ለልጅ ልጁም ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜም ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት እርሱን ያስገዙታል።
8 ለባቢሎን ንጉሥም ለናቡከደነፆር የማይገዛውን፥ ከባቢሎንም ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የማያደርገውን ሕዝብና መንግሥት፥ ያን ሕዝብ በእጁ እስካጠፋው ድረስ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እቀጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
9 እናንተ ግን። ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም የሚሉአችሁን ነቢያቶቻችሁንና ምዋርተኞቻችሁን፥ ሕልም አላሚዎቻችሁንና ቃላተኞቻችሁን መተተኞቻችሁንም አትስሙ፤
10 ከምድራቸሁ እንዲያርቁአችሁ፥ እኔም እንዳሳድዳችሁ እናንተም እንድትጠፉ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና።
11 ነገር ግን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የሚያደርገውንና የሚገዛለትን ሕዝብ በአገሩ ላይ እተወዋለሁ፤ እነርሱም ያርሱአታል ይቀመጡባትማል።
12 ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስም በዚህ ቃል ተናገርሁ። ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገታችሁን ዝቅ አድርጉ ለእርሱና ለሕዝቡም ተገዙላቸው በሕይወትም ኑሩ።
13 ለባቢሎን ንጉሥ ይገዛ ዘንድ እንቢ ስላለ ሕዝብ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ፥ አንተና ሕዝብህ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ለምን ትሞታላችሁ?
14 ሐሰተኛን ትንቢት ይናገሩላችኋልና። ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም የሚሉአችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ።
15 እኔ አልላክኋቸውምና፤ ነገር ግን እኔ እንዳሳድዳችሁ፥ እናንተና ትንቢት የሚናገሩላችሁ ነቢያትም እንድትጠፉ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
16 ለካህናትም ለዚህም ሕዝብ እንዲህ ብዬ ተናገርሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሐሰተኛውን ትንቢት ይናገሩላችኋልና። የእግዚአብሔር ቤት ዕቃ በቅርብ ጊዜ ከባቢሎን ይመለሳል የሚሉአችሁን የነቢያቶቻችሁን ቃል አትስሙ።
17 እነርሱም አትስሙ፤ ለባቢሎን ንጉሥ ተገዙ በሕይወትም ኑሩ። ይህችስ ከተማ ስለ ምን ባድማ ትሆናለች?
18 እነርሱ ግን ነቢያት ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔርም ቃል በእነርሱ ዘንድ ቢገኝ፥ በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት በኢየሩሳሌምም የቀረችው ዕቃ ወደ ባቢሎን እንዳትሄድ ወደ ሠራዊት ጌታ ወደ እግዚአብሔር ይማለሉ።
19 -
20 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ከበርቴዎች ሁሉ ማርኮ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ባፈለሳቸው ጊዜ ስላልወሰዳቸው ዓምዶች ስለ kWreውም ስለ መቀመጫዎቹም በዚህችም ከተማ ስለ ቀረች ዕቃ ሁሉ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤
21 በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት በኢየሩሳሌምም ስለ ቀረችው ዕቃ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
22 ወደ ባቢሎን ትወሰዳለች እስከምጐበኛትም ቀን ድረስ በዚያ ትኖራለች፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በዚያን ጊዜም አወጣታለሁ ወደዚህም ስፍራ እመልሳታለሁ።