ምዕራፍ 32

በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በአሥረኛው ዓመት፥ በናቡክደነፆር በአሥራ ስምንተኛው ዓመት፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው።
2 በዚያን ጊዜም የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ ነበር፤ ነቢዩም ኤርምያስ በይሁዳ ንጉሥ ቤት በነበረው በግዞት ቤት አደባባይ ታስሮ ነበር።
3 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ እንዲህ ብሎ አስጠብቆት ነበርና። ስለ ምን እንዲህ ብለህ ትንቢት ትናገራለህ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ እርሱም ይይዛታል፤
4 የይሁዳም ንጉሥ ሴዴቅያስ በእውነት በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፎ ይሰጣል፥ አፍ ለአፍም ይናገረዋል፥ ዓይኑም ዓይኑን ያያል እንጂ ከከለዳውያን እጅ አያመልጥም፤
5 እርሱም ሴዴቅያስን ወደ ባቢሎን ያፈልሰዋል፥ እኔም እስክጐበኘው ድረስ በዚያ ይኖራል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከከላዳውያን ጋር ብትዋጉ ምንም አትረቡም።
6 ኤርምያስም እንዲህ አለ። የእግዚአብሄር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
7 እነሆ፥ የአጐትህ የሰሎም ልጅ አናምኤል ወደ አንተ መጥቶ። ትገዛው ዘንድ መቤዠቱ የአንተ ነውና በዓናቶት ያለውን እርሻዬን ግዛ ይልሃል።
8 እንደ እግዚአብሔርም ቃል የአጐቴ ልጅ አናምኤል እኔ ወዳለሁበት ወደ ግዞቱ ቤት አደባባይ መጥቶ። በብንያም አገር በዓናቶት ያለውን እርሻዬን፥ እባክህ፥ ግዛ፤ ርስቱ የአንተ ነውና፥ መቤዠቱም የአንተ ነውና፤ ለአንተ ግዛው አለኝ። ይህም የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሆነ አወቅሁ።
9 በዓናቶትም ያለውን እርሻ ከአጐቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፥ አሥራ ሰባት ሰቅል ብርም መዘንሁለት።
10 በውሉም ወረቀት ላይ ፈረምሁ አተምሁትም፥ ምስክሮችንም ጠርቼ ብሩን በሚዛን መዘንሁለት።
11 የታተመውንና የተከፈተውን የውል ወረቀት ወሰድሁ፤
12 የአጐቴም ልጅ አናምኤል፥ የውሉንም ወረቀት የፈረሙ ምስክሮች፥ በግዞትም ቤት አደባባይ የተቀመጡ አይሁድ ሁሉ እያዩ የውሉን ወረቀት ለመሕሤያ ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት።
13 በፊታቸውም እንዲህ ብዬ ባሮክን አዘዝሁት።
14 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ብዙ ቀን ይጠበቁ ዘንድ የታተመውንና የተከፈተውን ይህን የውል ወረከት ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኑራቸው።
15 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ሰዎች በዚህች ምድር ቤትንና እርሻን የወይን ቦታንም እንደ ገና ይገዛሉ።
16 ለኔርያ ልጅ ለባሮክም የውሉን ወረቀት ከሰጠሁት በኋላ፥ እንዲህ ብዬ ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ።
17 አቤቱ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ሰማይንና ምድርን በታላቅ ኃይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፥ ከአንተም የሚያቅት ነገር የለም።
18 ለብዙ ሺህ ምሕረት ታደርጋለህ፥ የአባቶችንም በደል ከእነርሱ በኋላ በልጆቻቸው ብብት ትመልሳለህ፤ ስምህ ታላቅና ኃያል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
19 በምክር ታላቅ በሥራም ብርቱ ነህ፤ ለሁሉም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ፍሬ ትሰጥ ዘንድ ዓይኖችህ በአዳም ልጆች መንገድ ሁሉ ተገልጠዋል።
20 እስከ ዛሬም ድረስ ምልክትንና ድንቅን ነገር በግብጽ ምድር ደግሞም በእስራኤልና በሌሎች ሰዎች መካከል አድርገሃል፥ እንደ ዛሬም ለአንተ ስም አድርገሃል።
21 በምልክትና በድንቅ ነገር፥ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ በታላቅም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብጽ ምድር አወጣህ።
22 ትሰጣቸውም ዘንድ ለአባቶቻቸው የማልህላቸውን ምድር፥ ወተትና ማርንም የምታፈስሰውን ምድር፥ ሰጠሃቸው፤
23 እነርሱም ገብተው ወረሱአት፤ ነገር ግን ቃልህን አልሰሙም በሕግህም አልሄዱም፥ ያደረርም ዘንድ ካዘዝሃቸው ሁሉ ምንም አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣህባቸው።
24 እነሆ የአፈር ድልድል፥ ሊይዙአትም እስከ ከተማይቱ ድረስ ቀርበዋል፤ ከሰይፍና ከራብ ከቸነፈርም የተነሣ ከተማይቱ ለሚዋጉአት ለከለዳውያን እጅ ተሰጥታለች፥ የተናገርኸውም ሆኖአል፤ እነሆም፥ አንተ ታየዋለህ።
25 አንተም፥ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ። እርሻውን በብር ግዛ ምስክሮችንም ጥራ አልኸኝ፤ ከተማይቱ ግን ለከለዳውያን እጅ ተሰጥታለች።
26 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ።
27 እነሆ፥ እኔ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤
28 በውኑ እኔን የሚያቅተኝ ነገር አለን? ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ይህችን ከተማ ለከለዳውያን እጅና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እርሱም ይይዛታል።
29 ይህችን ከተማ የሚወጉ ከለዳውያን መጥተው በእሳት ያነድዱአታል፥ ያስቈጡኝም ዘንድ በሰገነታቸው ላይ ለበኣል ካጠኑባቸው፥ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቍርባን ካፈሰሱባቸው ቤቶች ጋር ያቃጥሉአታል።
30 የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች ከታናሽነታቸው ጀምሮ በፊቴ ክፉ ነገርን ብቻ አድርገዋልና፤ የእስራኤልም ልጆች እኔን በእጃቸው ሥራ ከማስቈጣት በቀር ሌላ ሥራ አላደረጉምና።
31 ከፊቴ አስወግዳት ዘንድ ይህች ከተማ ከሠሩአት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ቍጣዬንና መዓቴን ለማነሣሣት ሆናለችና፤
32 ይህም እኔን ያስቈጡኝ ዘንድ፥ እነርሱና ነገሥታቶቻቸው አለቆቻቸውም ካህናቶቻቸውም ነቢያቶቻቸውም የይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም የሚንኖሩ፥ ስላደረጉት ስለ እስራኤል ልጆችና ስለ ይሁዳ ልጆች ክፋት ሁሉ ነው።
33 ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ወደ እኔ መለሱ፤ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ሳሰተምራቸው ተግሣጽን ይቀበሉ ዘንድ አልሰሙም።
34 ያረክሱትም ዘንድ ስሜ በተጠራበት ቤት ውስጥ ርኵሰታቸውን አኖሩ።
35 ይሁዳን ወደ ኃጢአት እንዲያገቡት፥ ይህንን ርኵሰት ያደርጉ ዘንድ፥ እኔ ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን ነገር፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሎክ በእሳት ያሳልፉ ዘንድ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ያሉትን የበኣልን የኮረብታውን መስገጃዎች ሠሩ።
36 አሁን እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር አንተ ስለ እርስዋ። በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ተሰጥታለች ስለምትላት ከተማ እንዲህ ይላል።
37 እነሆ፥ በቍጣዬና በመዓቴ በታላቅም መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁባት አገር ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፥ ተዘልለውም እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤
38 እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
39 ለእነርሱም ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ ለዘላለም እንዲፈሩኝ አንድ ልብና አንድ መንገድ እሰጣቸዋለሁ።
40 ለእነርሱም ከማደርገው በጎነት አልመለስም ስል፥ ከእነርሱ ጋር የዘላለምን ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከእኔም ዘንድ ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ።
41 ለእነርሱም መልካምን በማድረግ ደስ ይለኛል በእውነትም በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ።
42 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ይህን እጅግ ክፉ ነገር ሁሉ በዚህ ሕዝብ ላይ እንዳመጣሁ፥ እንዲሁ የተናገርሁላቸውን በጎነት ሁሉ አመጣላቸዋለሁ።
43 እናንተም። ያለ ሰውና ያለ እንሰሳ ያለች ባድማ ናት፥ ለከለዳውያንም እጅ ተሰጥታለች በምትሉአት ምድር እርሻን ይገዛሉ።
44 ምርኮኞቻቸውንም እመልሳለሁና በብንያም አገር በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች በደጋውም ባሉ ከተሞች በቈላውም ባሉ ከተሞች በደቡብም ባሉ ከተሞች፥ ሰዎች እርሻውን በብር ይገዛሉ በውሉም ወረቀት ፈርመው ያትማሉ ምስክሮችንም ይጠራሉ።