ምዕራፍ 36

እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ።
2 አንድ የመጽሐፍ ክርታስ ውሰድ፥ ለአንተም ከተናገርሁበት ቀን ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተናገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት።
3 ምናልባት የይሁዳ ቤት። እኔ አደርግባቸዋለሁ ያልሁትንና ያሰብሁትን ክፉ ነገር ሁሉ ይሰሙ ይሆናል፥ ከክፋ መንገዳቸው ይመለሱ ዘንድ እኔም በደላቸውንና ኃጢአታቸውን ይቅር እል ዘንድ።
4 ኤርምያስም የኔርያን ልጀ ባሮክን ጠራ፥ ባሮክም እግዚአብሔር ለእርሱ የተናገረውን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ በመጽሐፉ ክርታስ ጻፈ።
5 ኤርምያስም ባሮክን እንዲህ ሲል አዘዘው። እኔ ተግዤአለሁ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤት እገባ ዘንድ አልችልም።
6 አንተ ግን ሂድ፥ ከአፌም የጻፍኸውን የእግዚአብሔርን ቃል በጾም ቀን በእግዚአብሔር ቤት በሕዝቡ ጆር በክርታሱ አንብብ፤ ደግሞም ከከተሞቻቸው በሚወጡ በይሁዳ ሰዎች ሁሉ ጆሮ አንብበው።
7 እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቍጣውና መዓቱ ታላቅ ነውና ምናልባት ጸሎታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትወድቅ ይሆናል፥ ሁሉም ከክፉ መንገዱ ይመለስ ይሆናል።
8 የኔርያም ልጅ ባሮክ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ቤት የእግዚአብሔርን ቃል በመጽሐፉ አነበበ።
9 እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአምስተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር በኢየሩሳሌም የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ ከይሁዳም ከተሞች ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ለመጾም አዋጅ ነገሩ።
10 ባሮክም የኤርምያስን ቃል በእግዚአብሄር ቤት በላይኛው አደባባይ በእግዚአብሔር ቤት በአዲሱ በር መግቢያ ባለው በጸሐፊው በሳፋን ልጅ በገማርያ ጓዳ በሕዝቡ ሁሉ ጆሮ በመጽሐፉ አነበበ።
11 የሳፋንም ልጅ የገማርያ ልጅ ሚክያስ የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመጽሐፉ በሰማ ጊዜ፥
12 ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ጸሐፊው ጓዳ ወረደ፤ እነሆም፥ አለቆች ሁሉ፥ ጸሐፊው ኤሊሳማ፥ የሸማያ ልጅ ድላያ፥ የዓክቦር ልጅ ኤልናታን፥ የሳፋን ልጅ ገማርያ፥ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ አለቆቹም ሁሉ በዚያ ተቀምጠው ነበር።
13 ሚክያስም ባሮክ በሕዝቡ ጆሮ በመጽሐፉ ባነበበ ጊዜ የሰማውን ቃል ሁሉ ነገራቸው።
14 አለቆቹም ሁሉ። በሕዝቡ ጆሮ ያነበብኸውን ክርታስ በእጅህ ይዘህ ና የሚል መልእክት በኵሲ ልጅ በሰሌምያ ልጅ በናታንያ ልጅ በይሁዲ እጅ ወደ ባሮክ ላኩ። የኔርያም ልጅ ባሮክ ክርታሱን በእጁ ይዞ ወደ እነርሱ መጣ።
15 እነርሱም። እስኪ ተቀመጥ፥ በጆሮአችንም አንብብ አሉት። ባሮክም በጆሮአቸው አነበበው።
16 ቃሉንም ሁሉ በሰሙ ጊዜ ፈርተው እርስ በእርሳቸው ተመካከሩ፥ ባሮክንም። ይህን ቃል ሁሉ በእርግጥ ለንጉሡ እንናገራለን አሉት።
17 ባሮክንም። ይህን ቃል ሁሉ ከአፉ እንዴት እንደ ጻፍኸው ንገረን ብለው ጠየቁት።
18 ባሮክም። ይህን ቃል ከአፉ ይነግረኝ ነበር፥ እኔም በመጽሐፉ ላይ በቀለም እጽፍ ነበር ብሎ መለሰላቸው።
19 አለቆቹም ባሮክን። አንተና ኤርምያስ ሂዱ፥ ተሸሸጉ፥ ወዴትም እንደ ሆናችሁ ማንም አይወቅ አሉት።
20 ወደ ንጉሡም ወደ አደባባይ ገቡ፥ ክርታሱንም በጸሐፊው በኤሊሳማ ጓዳ አኑረውት ነበር፤ ቃሉንም ሁሉ በንጉሡ ጆሮ ተናገሩ።
21 ንጉሡም ክርታሱን ያመጣ ዘንድ ይሁዲን ላከ፥ እርሱም ከጸሐፊው ከኤሊሳማ ጓዳ ወሰደው፤ ይሁዲም በንጉሡና በንጉሡ አጠገብ በቆሙት አለቆች ሁሉ ጆሮ አነበበው።
22 ንጉሡም በዘጠነኛው ወር በክረምት ቤት ተቀምጦ ነበር፥ በፊቱም በምድጃ ውስጥ እሳት ይነድድ ነበር።
23 ይሁዲም ሦስት ወይም አራት ዓምድ ያህል ባነበበ ቍጥር፥ ንጉሡ በካራ ቀደደው፤ ክርታሱም በምድጃ ውስጥ ባለው እሳት ፈጽሞ እስኪቃጠል ድረስ በምድጃ ውስጥ ወዳለው እሳት ጣለው።
24 ንጉሡም ይህንም ቃል ሁሉ የሰሙ ባሪያዎቹ ሁሉ አልፈሩም ልብሳቸውንም አልቀደዱም።
25 ነገር ግን ኤልናታንና ድላያ ገማርያም ክርታሱን እንዳያቃጥል ንጉሡን ለመኑት፥ እርሱ ግን አልሰማቸውም።
26 ንጉሡም ጸሐፊውን ባሮክንና ነቢዩን ኤርምያስን ይይዙ ዘንድ የንጉሡን ልጅ ይረሕምኤልንና የዓዝርኤልን ልጅ ሠራያን የዓብድኤልንም ልጅ ሰሌምያን አዘዘ፥ እግዚአብሔር ግን ሰወራቸው።
27 ንጉሡም ክርስታሱንና ባሮክ ከኤርምያስ አፍ የጻፈውን ቃል ካቃጠለ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ።
28 ዳግመኛም ሌላ ክርታስ ውሰድ፥ የይሁዳም ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው ክርታስ ላይ የነበረውን የቀድሞውን ቃል ሁሉ ጻፍበት።
29 የይሁዳንም ንጉሥ ኢዮአቄምን እንዲህ በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አንተ። የባቢሎን ንጉሥ በእርግጥ ይመጣል ይህችንም አገር ያፈርሳታል ከሰውና ከእንስሳም ባዶ ያደርጋታል ብለህ ለምን ጻፍህበት? ብለህ ይህን ክርታስ አቃጥለሃል።
30 ስለዚህም ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮአቄም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀማጭ አይኖርለትም፥ ሬሳውም በቀን ለትኩሳት በሌሊትም ለውርጭ ይጣላል።
31 ስለ ኃጢአታቸውም እርሱንና ዘሩን ባሪያዎቹንም እቀጣለሁ፤ እነርሱም አልሰሙምና የተናገርሁባቸውን ክፉ ነገር ሁሉ በእነርሱ ላይና በኢየሩሳሌም በሚቀመጡ በይሁዳም ሰዎች ላይ አመጣለሁ።
32 ኤርምያስም ሌላ ክርታስ ወሰደ ለኔርያም ልጅ ለጸሐፊው ለባሮክ ሰጠው፤ እርሱም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በእሳት ያቃጠለውን የመጽሐፉን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ ጻፈበት፥ ደግሞም እንደ ቀድሞው ያለ ቃል ብዙ ቃል ተጨመረበት።