ምዕራፍ 5

በኢየሩሳሌም መንገድ እየተመላለሳችሁ ሩጡ፥ ተመልከቱም፥ እወቁም፥ በአደባባይዋም ፈልጉ፤ ፍርድን የሚያደርገውን እውነትንም የሚሻውን ሰው ታገኙ እንደሆነ ይቅር እላታለሁ።
2 እነርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! ቢሉ የሚምሉት በሐሰት ነው።
3 አቤቱ፥ ዓይንህ እውነትን የምትመለከት አይደለችምን? አንተ ቀሥፈሃቸዋል ነገር ግን አላዘኑም፥ ቀጥቅጠሃቸውማል ነገር ግን ተግሣጽን እንቢ አሉ፤ ፊታቸውን ከድንጋይ ይልቅ አጠንክረዋል፤ ይመለሱ ዘንድ እንቢ አሉ።
4 እኔም። የእግዚአብሔርን መንገድና የአምላካቸውን ሕግ አላወቁምና እነዚህ በእውነት ድሆችና ሰነፎች ናቸው፤
5 ወደ ታላላቆቹ እሄዳለሁ እናገራቸውማለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንገንድና የአምላካቸውን ሕግ ያውቃሉና አልሁ። እነዚህ ግን ቀንበሩን በአንድነት ሰብረዋል፥ እስራቱንም ቈርጠዋል።
6 ስለዚህ ኃጢአታቸው በዝቶአልና፥ የክዳታቸውም ብዛት ጸንቶአልና ስለዚህ አንበሳ ከዱር ወጥቶ ይሰብራቸዋል፥ የበረሀም ተkWla ያጠፋቸዋል፥ ነብርም በከተሞቻቸው ላይ ይተጋል፥ ከዚያም የሚወጣ ሁሉ ይነጠቃል።
7 በእነዚህ ነገሮች ይቅር የምልሽ እንዴት አድርጌ ነው? ልጆችሽ ትተውኛል አማልክትም ባልሆኑ ምለዋል፤ ካጠገብኋቸውም በኋላ አመነዘሩ በጋለሞቶቹም ቤት ተሰበሰቡ።
8 እንደ ተቀለቡ ፈረሶች ሆኑ፤ እያንዳንዳቸውም ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ኋላ አሽካኩ።
9 በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን?
10 ወደ ቅጥርዋ ወጥታችሁ አፍርሱ፥ ነገር ግን ፈጽማችሁ አታጥፉ፤ ለእግዚአብሔር አይደሉምና ቅርንጫፍዋን ውሰዱ።
11 የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት በእኔ ላይ እጅግ ወንጅለዋል ይላል እግዚአብሔር።
12 እነርሱም። እርሱ አይደለም፥ ክፉ ነገርም አይመጣብንም ሰይፍንና ራብንም አናይም፤ ነቢያትም ነፋስ ይሆናሉ፥
13 የእግዚአብሔርም ቃል በእነርሱ ዘንድ የለም፥ እንዲህም ይደረግባቸዋል ብለው እግዚአብሔርን ክደዋል።
14 ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህ ቃል ተናግራችኋልና እነሆ፥ በአፍህ ውስጥ ቃሌን እሳት ይህንም ሕዝብ እንጨት አደርጋለሁ፥ ትበላቸውማለች።
15 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እነሆ፥ ሕዝብን ከሩቅ አመጣባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃያል ጥንታዊ ሕዝብ ነው፥ ቋንቋቸውንም የማታውቀው የሚናገሩትንም የማታስተውለው ሕዝብ ነው።
16 የፍላጻቸውም ሰገባ እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ ሁሉም ኃያላን ናቸው።
17 መከርህንና እንጀራህን ይበላሉ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህንም ይበሉአቸዋል፤ በጎችህንና ላሞችህንም ይበላሉ፤ ወይንህንና በለስህንም ይበላሉ፤ የምትታመናቸውን የተመሸጉ ከተሞችን በሰይፍ ይደበድባሉ።
18 ነገር ግን በዚያ ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ፈጽሜ አላጠፋችሁም።
19 እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ። አምላካችን እግዚአብሔር ይህን ነገር ሁሉ ስለምን አደረገብን? ብትሉ፥ አንተ። እንደ ተዋችሁኝ በአገራችሁም ሌሎችን አማልክት እንዳመለካችሁ፥ እንዲሁ ለእናንተ ባልሆነ አገር ለሌሎች ሰዎች ትገዛላችሁ ትላቸዋለህ።
20 ይህን በያዕቆብ ቤት አውሩ፥ በይሁዳም አሰሙ።
21 እናንተ ሰነፎች ልበ ቢሶች፥ ዓይን እያላችሁ የማታዩ፥ ጆሮም እያላችሁ የማትሰሙ ሕዝብ ሆይ፥ ይህን ስሙ።
22 በውኑ እኔን አትፈሩምን? ከፊቴስ አትደነግጡምን? ይላል እግዚአብሔር፤ እንዳያልፍ አሸዋን በዘላለም ትእዛዝ ለባሕር ዳርቻ አድርጌአለሁ፤ ሞገዱም ቢናወጥ አያሸንፍም፥ ቢጮኽም አያልፍበትም።
23 ለዚህ ሕዝብ ግን የሸፈተና ያመፀ ልብ አላቸው፤ ዐምፀዋል ሄደውማል።
24 በልባቸውም። የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ በጊዜው የሚሰጠውን፥ ለመከርም የተመደቡትን ወራት የሚጠብቅልንን አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፍራ አላሉም።
25 በደላችሁ እነዚህን አስቀርታለች፥ ኃጢአታችሁም መልካምን ነገር ከለከለቻችሁ።
26 በሕዝቤ መካከል ክፉዎች ሰዎች ተገኝተዋል፤ እንደ አጥማጆችም ያደባሉ፥ ወጥመድንም ይዘረጋሉ ሰዎችንም ያጠምዳሉ።
27 ቀፎ ወፎችን እንደሚሞላ፥ እንዲሁ ቤታቸው ሽንገላን ሞልታለች፤እንዲሁም ከብረዋል ባለ ጠጎችም ሆነዋል።
28 ወፍረዋል ሰብተውማል፥ ክፋታቸውንም ያለ ልክ አብዝተዋል፤ የድሀ አደጎች ነገር መልካም እንዲሆን አልተምዋገቱላቸውም፥ የችግረኞችንም ፍርድ አልፈረዱላቸውም።
29 በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን?
30 የምታስደንቅና የምታስደነግጥ ነገር በምድር ላይ ሆናለች፤
31 ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፥ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፥ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወድዳሉ፤ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ?