ትንቢተ ኤርምያስ
ምዕራፍ 29
ነቢዩ ኤርምያስ ወደ ተረፉት የምርኮ ሽማግሌዎች፥ ወደ ካህናቱም፥ ወደ ነቢያቱም፥ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ወዳፈለሰውም ሕዝብ ሁሉ ከኢየሩሳሌም የላከው የደብዳቤው ቃል ይህ ነው።
2 ይህም የሆነው ንጉሡ ኢኮንያን እናቱም እቴጌይቱ ጃንደረቦቹም የይሁዳና የኢየሩሳሌምም አለቆች ጠራቢዎችና ብረት ሠራተኞችም ከኢየሩሳሌም ከወው በኋላ ነው።
3 ኤርምያስ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር ወደ ባቢሎን በላካቸው በሳፋን ልጅ በኤልዓሣና በኬልቅያስ ልጅ በገማርያ እጅ ደብዳቤውን እንዲህ ሲል ላከው።
4 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረክኋቸው ምርኮኞች ሁሉ እንዲህ ይላል።
5 ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፥ አታክልትም ተክላችሁ ፍሬዋን ብሉ፤
6 ተጋቡ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ውለዱ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁንም አጋቡ፥ እነርሱም ወንዶችንና ሴቶችን ልጆች ይውለዱ፤ ከዚያም ተባዙ ጥቂቶችም አትሁኑ።
7 በእርስዋ ሰላም ሰላም ይሆንላችኋልና ወደ እርስዋ ላስማርክኋችሁ ከተማ ሰላምን ፈልጉ፥ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ።
8 የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በመካከላችሁ ያሉት ነቢያቶቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፥ እናንተም የምታልሙትን ሕልም አትስሙ።
9 በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና፤ እኔም አልላክኋቸውም።
10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ሰባው ዓመት በባቢሎን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፥ ወደዚህም ስፍራ እመልሳችሁ ዘንድ መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ።
11 ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም።
12 እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ።
13 እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ።
14 ከእናንተም ዘንድ እገኛለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፥ ከአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እናንተንም ካሳደድሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተንም ለምርኮ ወዳፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ።
15 እናንተም። እግዚአብሔር በባቢሎን ነቢያትን አስነሥቶልናል ብላችኋልና፤
16 እግዚአብሔር በዳዊት ዙፋን ስለ ተቀመጠ ንጉሥ ከእናንተም ጋር ስላልተማረኩት ወንድሞቻችሁ፥ በዚህች ከተማ ስለሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ፥ እንዲህ ይላልና።
17 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም እሰድድባቸዋለሁ፥ ከክፋቱም የተነሣ ይበላ ዘንድ እንደማይቻል እንደ ክፉ በለስ አደርጋቸዋለሁ።
18 በሰይፍም በራብም በቸነፈርም አሳዳድዳቸዋለሁ፥ ባሳደድሁባቸውም አሕዛብ ሁሉ ዘንድ ለጥላቻና ለመደነቂያ ለማፍዋጫም ለመሰደቢያም እንዲሆኑ በምድር መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለመበተን አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።
19 ይህም የሆነው ቃሌን ስላልሰሙ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በማለዳ ተነሥቼ ባሪያዎቼን ነቢያትን ወደ እነርሱ ሰድጃለሁና፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
20 ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን የሰደድኋችሁ ምርኮኞች ሁሉ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
21 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ስለሚናገሩላችሁ ስለ ቆላያ ልጅ ስለ አክዓብና ስለ መዕሤያ ልጅ ስለ ሴዴቅያስ እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፥ በዓይኖቻችሁም ፊት ይገድላቸዋል።
22 ከእነርሱም የተነሣ በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ። የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ እግዚአብሔር ያድርግህ የምትባል እርግማንን ያነሣሉ፤ እኔም አውቃለሁ ምስክርም ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር።
23 በእስራኤል ዘንድ ስንፍና አድርገዋልና፥ ከባልንጀሮቻቸውም ሚስቶች ጋር አመንዝረዋልና፥ ያላዘዝኋቸውንም ቃል በስሜ በሐሰት ተናግረዋልና።
24 ለኔሔላማዊው ለሸማያ እንዲህ በል።
25 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በኢየሩሳሌም ወዳለው ሕዝብ ሁሉ፥ ወደ ካህኑም ወደ መዕሤያ ልጅ ወደ ሶፎንያስ፥ ወደ ካህናቱም ሁሉ ደብዳቤዎችን በስምህ እንዲህ ስትል ልከሃል።
26 እያበደ ትንቢት የሚናገርን ሰው ሁሉ በእግር ግንድና በዛንጅር ታኖረው ዘንድ በእግዚአብሔር ቤት አለቃ እንድትሆን እግዚአብሔር በካህኑ በዮዳሄ ፋንታ ካህን አድርጎሃል።
27 አሁንስ ትንቢት ተናጋሪውን የዓናቶቱን ሰው ኤርምያስን ስለ ምን አትዘልፈውም?
28 እርሱ። ምርኮው የረዘመው ነውና ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፥ አታክልትንም ተክላችሁ ፍሬዋን ብሉ ብሎ ወደ እኛ ወደ ባቢሎን ልኮአልና።
29 ካህኑም ሶፎንያስ ይህን ደብዳቤ በነቢዩ በኤርምያስ ጆሮ አነበበው።
30 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ።
31 እግዚአብሔር ስለ ኔሔላማዊው ስለ ሸማያ እንዲህ ይላል ብለህ ወደ ምርኮኞች ሁሉ ላክ። እኔ ሳልልከው ሸማያ ትንቢት ተናግሮላችኋልና፥ በሐሰትም እንድትታመኑ አድርጎአችኋልና፤
32 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ኔሔላማዊውን ሸማያንና ዘሩን እቀጣለሁ፤ እኔም የማደርግላችሁን መልካሙን ነገር የሚያይ ሰው በመካከላችሁ አይኖርላችሁም