ምዕራፍ 16

የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም አይሁኑልህ።
3 እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ስለ ተወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፥ ስለወለዱአቸውም ስለ እናቶቻቸው፥ በዚህችም ምድር ስለ ወለዱአቸው ስለ አባቶቻቸው እንዲህ ይላልና።
4 በክፉ ሞት ይሞታሉ፤ አይለቀስላቸውም አይቀበሩምም፥ በመሬትም ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ፤ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፥ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናሉ።
5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰላሜን፥ ቸርነትና ምሕረትን፥ ከዚህ ሕዝብ አስወግጄአለሁና ልቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፥ ታለቅስም ታዝንም ዘንድ አትሂድ።
6 ታላላቆችና ታናናሾች በዚህች ምድር ይሞታሉ፤ አይቀበሩም ሰዎችም አያለቅሱላቸውም ስለ እነርሱም ገላን አይነጩላቸውም ራስንም አይላጩላቸውም፤
7 ሰዎችም ስለ ሞቱት ለማጽናናት የእዝን እንጀራ አይቈርሱላቸውም፥ ስለ አባታቸውና ስለ እናታቸውም የመጽናናት ጽዋ አያጠጡአቸውም።
8 ትበላና ትጠጣ ዘንድ ከእነርሱ ጋር ለመቀመጥ ወደ ግብዣ ቤት አትግባ።
9 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ በዓይናችሁ ፊት በዘመናችሁም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስቀራለሁ።
10 ለዚህም ሕዝብ ይህን ቃል ሁሉ በተናገርህ ጊዜ። ይህን ሁሉ ታላቅ የሆነ ክፉ ነገርን ስለ ምን እግዚአብሔር ተናገረብን? በደላችንስ ምንድር ነው? በአምላካችንስ በእግዚአብሔር ላይ የሠራነው ኃጢአታችን ምንድር ነው? ቢሉህ፥
11 አንተ እንዲህ ትላቸዋለህ። አባቶቻችሁ እኔን ስለ ተው ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ሌሎችንም አማልክት ተከተሉ አመለኩአቸውም ሰገዱላቸውም፥ እነርሱም ትተውኛል፥ ሕጌንም አልጠበቁም
12 ፤ እናንተም ከአባቶቻችሁ ይልቅ ክፉ አድርጋችኋል፤ እነሆም፥ ሁላችሁ እንደ ክፉ ልባችሁ እልከኝነት ሄዳችኋል እኔንም አልሰማችሁም።
13 ስለዚህ ከዚህች ምድር እናንተና አባቶቻችሁ ወዳላወቃችኋት ምድር እጥላችኋለሁ፤ ምሕረትንም አላደርግላችሁምና በዚያ ሌሎችን አማልክት ቀንና ሌሊት ታመልካላችሁ።
14 ስለዚህ፥ እነሆ። የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤
15 ነገር ግን።የእስራኤልን ልጆች ከሰሜን ምድር ካሳደዳቸውም ምድር ሁሉ ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ይባላል፤ እኔም ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ወደ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።
16 እነሆ፥ ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እሰድዳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እነርሱም ያጠምዱአቸዋል፤ ከዚያም በኋላ ብዙ አዳኞችን እሰድዳለሁ፥ እነርሱም ከየተራራውና ከየኮረብታው ሁሉ ከየድንጋዩም ስንጣቂ ውስጥ ያድኑአቸዋል።
17 ዓይኔ በመንገዳቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ከፊቴም አልተሰወሩም፥ ኃጢአታቸውም ከዓይኔ አልተሸሸገም።
18 ምድሬንም በተጠሉ በጣዖቶቻቸው ሬሳዎች አርክሰዋልና፥ ርስቴንም አስጸያፊ በሆኑ ነገሮች ሞልተዋልና አስቀድሜ የበደላቸውንና የኃጢአታቸውን ዕዳ ሁለት እጥፍ እከፍላቸዋለሁ።
19 አቤቱ፥ ኃይሌ፥ አምባዬ፥ በመከራም ቀን መጠጊያዬ ሆይ፥ ከምድር ዳርቻ አሕዛብ ወደ አንተ መጥተው። በእውነት አባቶቻችን ውሸትንና ከንቱን ነገር የማይረባቸውንም ወርሰዋል ይላሉ።
20 በውኑ ሰው አማልክት ያልሆኑትን ለራሱ አማልክትን አድርጎ ይሠራልን?
21 ስለዚህ፥ እነሆ፥ አስታውቃቸዋለሁ፥ በዚህች ጊዜ እጄንና ኃይሌን አስታውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ያውቃሉ።