ምዕራፍ 1

እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች። ከነዓናውያንን ለመውጋት ማን በፊት ይወጣልናል? ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ።
2 ፤ እግዚአብሔርም። ይሁዳ ይውጣ፤ እነሆ፥ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቻለሁ አለ።
3 ፤ ይሁዳም ወንድሙን ስምዖንን። ከነዓናውያንን እንወጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ወደ ዕጣዬ ውጣ፥ እኔም ደግሞ ከአንተ ጋር ወደ ዕጣህ እሄዳለሁ አለው። ስምዖንም ከእርሱ ጋር ሄደ።
4 ፤ ይሁዳም ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፥ ከእነርሱም በቤዜቅ ውስጥ አሥር ሺህ ሰዎች ገደሉ።
5 ፤ አዶኒቤዜቅንም በቤዜቅ አገኙትና ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንንም መቱአቸው።
6 ፤ አዶኒቤዜቅም ሸሸ፤ አሳድደውም ያዙት፥ የእጁንና የእግሩንም አውራ ጣት ቈረጡ።
7 ፤ አዶኒቤዜቅም። የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣት የተቈረጡ ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ በታች ፍርፋሪ ይለቅሙ ነበር፤ እኔ እንዳደረግሁ እግዚአብሔር እንዲሁ መለሰልኝ አለ። ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፥ በዚያም ሞተ።
8 ፤ የይሁዳም ልጆች ኢየሩሳሌምን ተዋግተው ያዙአት፥ በሰይፍ ስለትም መቱአት፥ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉአት።
9 ፤ ከዚያም በኋላ የይሁዳ ልጆች በተራራማው አገርና በደቡቡ በኩል በቈላውም ውስጥ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ሊወጉ ወረዱ።
10 ፤ ይሁዳም በኬብሮን የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ሊወጋ ሄደ። የኬብሮንም ስም አስቀድሞ ቂርያትአርባቅ ነበረ። ሴሲንና አኪመንን ተላሚንም ገደሉ።
11 ፤ ከዚያም የዳቤርን ሰዎች ሊወጋ ሄደ፤ አስቀድሞም የዳቤር ስም ቅርያትሤፍር ነበረ።
12 ፤ ካሌብም። ቅርያትሤፍርን ለሚመታና ለሚይዝ ልጄን ዓክሳን አጋባዋለሁ አለ።
13 ፤ የካሌብም ትንሽ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ያዛት፤ ልጁንም ዓክሳን አጋባው።
14 ፤ እርስዋም ወደ እርሱ በመጣች ጊዜ ከአባትዋ እርሻ እንዲለምን መከረችው። እርስዋም ከአህያዋ ወረደች፤ ካሌብም። ምን ፈለግሽ? አላት።
15 ፤ እርስዋም። በረከትን ስጠኝ፤ በደቡብ በኩል ያለውን ምድር ሰጥተኸኛልና የውኃ ምንጭ ደግሞ ስጠኝ አለችው። ካሌብም ላይኛውንና ታችኛውን ምንጭ ሰጣት።
16 ፤ የቄናዊው የሙሴ አማት ልጆችም ከይሁዳ ልጆች ጋር ዘንባባ ካለባት ከተማ ተነሥተው ከዓራድ በደቡብ በኩል ወዳለው ወደ ይሁዳ ምድረ በዳ ወጡ፤ ሄደውም ከሕዝቡ ጋር ተቀመጡ።
17 ፤ ይሁዳም ከወንድሙ ከስምዖን ጋር ሄደ፥ በጽፋት የተቀመጡትንም ከነዓናውያንን መቱ፥ ፈጽመውም አጠፉአት። የከተማይቱንም ስም ሔርማ ብለው ጠሩአት።
18 ፤ ይሁዳም ጋዛንና ዳርቻዋን፥ አስቀሎናንና ዳርቻዋን፥ አቃሮንንና ዳርቻዋን ያዘ።
19 ፤ እግዚአብሔርም ከይሁዳ ጋር ነበረ፤ ይሁዳም ተራራማውን አገር ወረሰ፤ በሸለቆው የሚኖሩት ግን የብረት ሰረገሎች ነበሩአቸውና ሊያወጣቸው አልቻለም።
20 ፤ ሙሴም እንደ ተናገረ ለካሌብ ኬብሮንን ሰጡት፤ ከዚያም ሦስቱን የዔናቅ ልጆች አወጣ።
21 ፤ ነገር ግን በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን የብንያም ልጆች አላወጡአቸውም፤ ኢያቡሳውያንም ከብንያም ልጆች ጋር እስከ ዛሬ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀምጠዋል።
22 ፤ የዮሴፍም ወገን ደግሞ በቤቴል ላይ ወጡ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበረ።
23 ፤ የዮሴፍም ወገን ቤቴልን የሚሰልሉ ላኩ። አስቀድሞም የከተማይቱ ስም ሎዛ ይባል ነበር።
24 ፤ ጠባቂዎቹም አንድ ሰው ከከተማ ሲወጣ አይተው። የከተማይቱን መግቢያ አሳየን፥ እኛም ቸርነት እናደርግልሃለን አሉት።
25 ፤ የከተማይቱንም መግቢያ አሳያቸው፥ ከተማይቱንም በሰይፍ ስለት መቱ፤ ያንን ሰውና ወገኖቹን ግን ለቀቁአቸው።
26 ፤ ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄደ፥ በዚያም ከተማን ሠራ፥ ስምዋንም ሎዛ ብሎ ጠራት። እስከ ዛሬም ድረስ ስምዋ ይህ ነው።
27 ፤ ምናሴም የቤትሳንንና የመንደሮችዋን፥ የታዕናክንና የመንደሮችዋን፥ የዶርንና የመንደሮችዋን፥ የይብለዓምንና የመንደሮችዋን፥ የመጊዶንና የመንደሮችዋን ሰዎች አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያ አገር በመቀመጥ ጸኑ።
28 ፤ እስራኤልም በበረቱ ጊዜ ከነዓናውያንን አስገበሩአቸው፥ ፈጽመውም አላወጡአቸውም።
29 ፤ ኤፍሬምም በጌዝር የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው በጌዝር ተቀመጡ።
30 ፤ ዛብሎንም የቂድሮንንና የነህሎልን ሰዎች አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው ተቀመጡ፥ ግብርም የሚገብሩለት ሆኑ።
31 ፤ አሴርም የዓኮንና የሲዶንን የአሕላብንም የአክዚብንም የሒልባንም የአፌቅንም የረአብንም ሰዎች አላወጣቸውም።
32 ፤ በዚያችም ምድር የተቀመጡትን ከነዓናውያን አላወጡአቸውምና በመካከላቸው የአሴር ልጆች ተቀመጡ።
33 ፤ ንፍታሌምም የቤትሳሚስንና የቤትዓናትን ሰዎች አላወጣቸውም፥ በምድሩም በተቀመጡት በከነዓናውያን መካከል ተቀመጡ፤ ነገር ግን የቤትሳሚስና የቤትዓናት ሰዎች ግብር የሚገብሩለት ሆኑ።
34 ፤ አሞራውያንም የዳንን ልጆች ወደ ተራራማው አገር እንዲያፈገፍጉ አስገደዱአቸው፥ ወደ ሸለቆውም እንዳይወርዱ ከለከሉአቸው።
35 ፤ አሞራውያን በሔሬስ ተራራና በኤሎን በሸዓልቢምም በመቀመጥ ጸኑ፤ ነገር ግን የዮሴፍ ቤት እጅ ከበደች፥ አስገበረቻቸውም።
36 ፤ የአሞራውያንም ድንበር ከአቅረቢም ዐቀበት ከጭንጫው ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ነበረ።