ምዕራፍ 8

የኤፍሬም ሰዎች። ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ምድያምን ለመዋጋት በወጣህ ጊዜ ለምን አልጠራኸንም? አሉት። ጽኑ ጥልም ተጣሉት።
2 ፤ እርሱም። እኔ ካደረግሁት እናንተ ያደረጋችሁት አይበልጥምን? የኤፍሬም ወይን ቃርሚያ ከአቢዔዝር ወይን መከር አይሻልምን?
3 ፤ እግዚአብሔር የምድያምን መኳንንት ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል፤ እናንተ ያደረጋችሁትን የሚመስል እኔ ምን ማድረግ እችል ኖሮአል? አላቸው። ይህን በተናገረ ጊዜ ቍጣቸው በረደ።
4 ፤ ጌዴዎንም ከሦስቱ መቶ ሰዎች ጋር ወደ ዮርዳኖስ ደርሶ ተሻገረ፤ ምንም እንኳ ቢደክሙ ያሳድዱ ነበር።
5 ፤ የሱኮትንም ሰዎች። የምድያምን ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን ሳሳድድ፥ ደክመዋልና እኔን ለተከተሉ ሕዝብ እንጀራ፥ እባካችሁ፥ ስጡ አላቸው።
6 ፤ የሱኮትም አለቆች። እኛ ለሠራዊትህ እንጀራ እንድንሰጥ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን? አሉ።
7 ፤ ጌዴዎንም። እግዚአብሔር ዛብሄልንና ስልማናን በእጄ አሳልፎ ሲሰጠኝ እኔ በምድረ በዳ እሾህና በኵርንችት ሥጋችሁን እገርፋለሁ አለ።
8 ፤ ከዚያም ወደ ጵኒኤል ወጣ፥ ለጵኒኤልም ሰዎች እንዲሁ አላቸው፤ የጵንኤልም ሰዎች የሱኮት ሰዎች እንደ መለሱ መለሱለት።
9 ፤ እርሱም የጵኒኤልን ሰዎች ደግሞ። በደኅና በተመለስሁ ጊዜ ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ ብሎ ተናገራቸው።
10 ፤ ዛብሄልና ስልማናም ከሠራዊቶቻቸው ጋር በቀርቀር ነበሩ፤ ሰይፍ የሚመዝዙ መቶ ሀያ ሺህ ሰዎች ወድቀው ነበርና ከምሥራቅ ሰዎች ሠራዊት ሁሉ የቀሩ አሥራ አምስት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ።
11 ፤ ጌዴዎንም የድንኳን ተቀማጮች ባሉበት መንገድ በኖባህና በዮግብሃ በምሥራቅ በኩል ወጣ፤ ሠራዊቱም ተዘልሎ ነበርና ሠራዊቱን መታ።
12 ፤ ዛብሄልና ስልማናም ሸሹ፤ እርሱም አሳደዳቸው፥ ሁለቱንም የምድያም ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን ያዘ፥ ሠራዊቱንም ሁሉ አስደነገጠ።
13 ፤ የኢዮአስ ልጅም ጌዴዎን ከሔሬስ ዳገት ከሰልፍ ተመለሰ።
14 ፤ ከሱኮትም ሰዎች አንድ ብላቴና ይዞ ጠየቀው፤ እርሱም የሱኮትን አለቆችና ሽማግሌዎች ሰባ ሳባት ሰዎች ጻፈለት።
15 ፤ ወደ ሱኮትም ሰዎች መጥቶ። ለደከሙት ሰዎችህ እንጀራ እንሰጥ ዘንድ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን? ብላችሁ የተላገዳችሁብኝ፥ ዛብሄልና ስልማና እነሆ፥ አለ።
16 ፤ የከተማይቱንም ሽማግሌዎች ያዘ፥ የምድረ በዳንም እሾህና ኵርንችት ወስዶ የሱኮትን ሰዎች ገረፋቸው።
17 ፤ የጵኒኤልንም ግንብ አፈረሰ፥ የከተማይቱንም ሰዎች ገደላቸው።
18 ፤ ዛብሄልንና ስልማናን። በታቦር የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ? አላቸው። እነርሱም። እንደ አንተ ያሉ ነበሩ፥ አንተንም ይመስሉ ነበር፤ መልካቸውም እንደ ንጉሥ ልጆች መልክ ነበረ ብለው መለሱለት።
19 ፤ እርሱም። የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ነበሩ፤ አድናችኋቸው ቢሆን ኖሮ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ አልገድላችሁም ነበር አለ።
20 ፤ በኵሩንም ዬቴርን። ተነሥተህ ግደላቸው አለው፤ ብላቴናው ግን ገና ብላቴና ነበረና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም።
21 ፤ ዛብሄልና ስልማናም። የሰው ኃይሉ እንደ ሰውነቱ ነውና አንተ ተነሥተህ ውደቅብን አሉት። ጌዴዎንም ተነሥቶ ዛብሄልንና ስልማናን ገደለ፥ በግመሎቻቸውም አንገት የነበሩትን ሥሉሴዎች ማረከ።
22 ፤ የእስራኤልም ሰዎች ጌዴዎንን። ከምድያም እጅ አድነኸናልና አንተ ልጅህም የልጅ ልጅህም ደግሞ ግዙን አሉት።
23 ፤ ጌዴዎንም። እኔ አልገዛችሁም፥ ልጄም አይገዛችሁም፤ እግዚአብሔር ይገዛችኋል አላቸው።
24 ፤ እስማኤላውያንም ስለ ነበሩ የወርቅ ጕትቻ ነበራቸውና ጌዴዎን። ሁላችሁ ከምርኮአችሁ ጕትቻችሁን እንድትሰጡኝ እለምናችኋለሁ አላቸው።
25 ፤ እነርሱም። ፈቅደን እንሰጥሃለን ብለው መለሱለት። መጎናጸፊያም አነጠፉ፥ ሰውም ሁሉ የምርኮውን ጕትቻ በዚያ ላይ ጣለ።
26 ፤ የለመነውም የወርቅ ጕትቻ ሚዛኑ፥ ከአምባሩ፥ ከድሪውም፥ የምድያምም ነገሥታት ከለበሱት ከቀዩ ቀሚስ፥ በግመሎቻቸውም አንገት ከነበሩት ሥሉሴዎች ሌላ፥ ሺህ ሰባት መቶ ሰቅለ ወርቅ ነበረ።
27 ፤ ጌዴዎንም ኤፉድ አድርጎ አሠራው፥ በከተማውም በዖፍራ አኖረው፤ እስራኤልም ሁሉ ተከትሎት አመነዘረበት፤ ለጌዴዎንና ለቤቱም ወጥመድ ሆነ።
28 ፤ ምድያምም በእስራኤል ልጆች ተዋረደ፥ ራሳቸውንም ዳግመኛ አላነሡም፤ በጌዴዎንም ዕድሜ ምድሪቱ አርባ ዓመት ዐረፈች።
29 ፤ የኢዮአስም ልጅ ይሩበኣል ሄዶ በቤቱ ተቀመጠ።
30 ፤ ለጌዴዎንም ብዙ ሚስቶች ነበሩትና ከወገቡ የወጡ ሰባ ልጆች ነበሩት።
31 ፤ በሴኬምም የነበረችው ቁባቱ ወንድ ልጅ ወለደችለት፥ ስሙንም አቤሜሌክ ብሎ ጠራው።
32 ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን በመልካም ሽምግልና ሞተ፥ በአቢዔዝራውያንም ከተማ በዖፍራ በነበረችው በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ።
33 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ጌዴዎን ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመለሱ፥ በኣሊምንም ተከትለው አመነዘሩ፤ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ።
34 ፤ የእስራኤልም ልጆች በዙሪያቸው ከነበሩት ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ ያዳናቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን አላሰቡትም፤
35 ፤ እርሱም ለእስራኤል በጎ ነገርን ሁሉ እንዳደረገ መጠን፥ እነርሱ ለጌዴዎን ለይሩበኣል ቤት ወረታ አላደረጉም።