ምዕራፍ 5

በዚያም ቀን ዲቦራና የአቢኒኤም ልጅ ባርቅ እንዲህ ብለው ተቀኙ።
2 ፤ በእስራኤል ውስጥ መሪዎች ስለ መሩ፥ ሕዝቡም ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ስለ ሰጡ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ።
3 ፤ ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፤ መኳንንት ሆይ፥ አድምጡ፤ እኔ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ።
4 ፤ አቤቱ፥ ከሴይር በወጣህ ጊዜ፥ ከኤዶምያስም ሜዳ በተራመድህ ጊዜ፥ ምድሪቱ ተናወጠች፥ ሰማያቱም አንጠበጠቡ፤ ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠበጠቡ።
5 ፤ ተራሮች ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ቀለጡ፥ ያም ሲና ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ።
6 ፤ በዓናት ልጅ በሰሜጋር ዘመን፥ በኢያዔል ዘመን መንገዶች ተቋረጡ፤ መንገደኞች በስርጥ መንገድ ይሄዱ ነበር።
7 ፤ አንቺ፥ ዲቦራ፥ እስክትነሽ ድረስ፥ ለእስራኤልም እናት ሆነሽ እስክትነሽ ድረስ፥ ኃያላን በእስራኤል ዘንድ አነሱ፥ አለቁም።
8 ፤ አዲሶች አማልክትን መረጡ፤ በዚያ ጊዜ ሰልፍ በበሮች ሆነ፤ በአርባ ሺህ በእስራኤል ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታየም።
9 ፤ ልቤ ወደ እስራኤል አለቆች ነው፥ በሕዝቡ መካከል ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ወደ ሰጡት፤ እግዚአብሔርን አመስግኑ።
10 ፤ በነጫጭ አህዮች ላይ የምትጫኑ፥ በወላንሳ ላይ የምትቀመጡ፥ በመንገድም የምትሄዱ፥ ተናገሩ።
11 ፤ በማጠጫው መካከል ካሉት ከቀስተኞች ጩኸት ርቀው፥ በዚያ የእግዚአብሔርን ጽድቅ፥ በእስራኤል ላይ የግዛቱን ጽድቅ ይጫወታሉ፤ ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ በሮች ወረዱ።
12 ፤ ንቂ፥ ንቂ፥ ዲቦራ ሆይ፤ ንቂ፥ ንቂ፥ ቅኔውን ተቀኚ፤ ባርቅ ሆይ፥ ተነሣ፤ የአቢኒኤም ልጅ ሆይ፥ ምርኮህን ማርክ።
13 ፤ በዚያ ጊዜ የቀሩት ወደ ኃያላኑና ወደ ሕዝቡ ወረዱ፤ እግዚአብሔርም ስለ እኔ በኃያላን ላይ ወረደ።
14 ፤ በአማሌቅ ዘንድ ሥር የነበራቸው እነርሱ ከኤፍሬም፥ ብንያም ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ከአንተ በኋላ ወረዱ፤ አለቆች ከማኪር፥ የንጉሥንም ዘንግ የሚይዙ ከዛብሎን ወረዱ።
15 ፤ የይሳኮርም አለቆች ከዲቦራ ጋር ነበሩ፤ ይሳኮርም እንደ ባርቅ ነበረ፤ ከእግሩ በኋላ ወደ ሸለቆው ቸኰሉ፤ በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ብዙ የልብ ማመንታት ነበረ።
16 ፤ መንጎች ሲያፍዋጩ ለመስማት በበጎች ጕረኖ መካከል ለምን ተቀመጥህ? በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ።
17 ፤ ገለዓድ በዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፤ ዳንም ለምን በመርከብ ውስጥ ቀረ? አሴርም በባሕሩ ዳር ተቀመጠ፥ በወንዞቹም ዳርቻ ዐረፈ።
18 ፤ ዛብሎን ነፍሱን ወደ ሞት ያሳለፈ ሕዝብ ነው፥ ንፍታሌምም በአገሩ ኮረብታ ላይ ነው።
19 ፤ ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፤ በዚያ ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፤ የብር ዘረፋም አልወሰዱም።
20 ፤ ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፤ በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ።
21 ፤ ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው። ነፍሴ ሆይ፥ በኃይል እርገጪ።
22 ፤ ከኃያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ።
23 ፤ የእግዚአብሔር መልአክ። ሜሮዝን እርገሙ፤ እግዚአብሔርን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥ እግዚአብሔርን ለመርዳት አልመጡምና የተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ።
24 ፤ የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፤ በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን።
25 ፤ ውኃ ለመነ፥ ወተትም ሰጠችው፤ በተከበረ ዳካ እርጎ አቀረበችለት።
26 ፤ እጅዋን ወደ ካስማ፥ ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፤ በመዶሻውም ሲሣራን መታች፥ ራሱንም ቸነከረች፤ ጆሮግንዱንም በሳች፥ ጎዳችውም።
27 ፤ በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ ተኛ፤ በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፤ በተደፋበት ስፍራ በዚያ ወድቆ ሞተ።
28 ፤ ከመስኮት ሆና ተመለከተች፤ የሲሣራ እናት በሰቅሰቅ ዘልቃ። ስለ ምን ለመምጣት ሰረገላው ዘገየ? ስለ ምንስ የሰረገላው መንኰራኵር ቈየ? ብላ ጮኸች።
29 ፤ ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፤ እርስዋ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች።
30 ፤ ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን? ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቈነጃጅት፤ ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፥ በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጕርጕር ልብስ።
31 ፤ አቤቱ፥ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፤ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፥ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች።