ምዕራፍ 12

የኤፍሬም ሰዎች ተሰበሰቡ፥ ወደ ጻፎንም ተሻግረው ዮፍታሔን። ከአሞን ልጆች ጋር ለመዋጋት ስታልፍ ከአንተ ጋር እንድንሄድ ስለ ምን አልጠራኸንም? ቤትህን በአንተ ላይ በእሳት እናቃጥለዋለን አሉት።
2 ፤ ዮፍታሔም። ከአሞን ልጆች ጋር ለእኔና ለሕዝቤ ጽኑ ጠብ ነበረን፤ በጠራኋችሁም ጊዜ ከእጃቸው አላዳናችሁኝም።
3 ፤ እንዳላዳናችሁኝም ባየሁ ጊዜ ነፍሴን በእጄ አድርጌ በአሞን ልጆች ላይ አለፍሁ፥ እግዚአብሔርም በእጄ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ለምንስ ዛሬ ልትወጉኝ ወደ እኔ መጣችሁ? አላቸው።
4 ፤ ዮፍታሔም የገለዓድን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፥ ከኤፍሬምም ጋር ተዋጋ፤ ኤፍሬምም። ገለዓዳውያን ሆይ፥ እናንተ በኤፍሬምና በምናሴ መካከል የተቀመጣችሁት ከኤፍሬም ሸሽታችሁ ነው ስላሉ የገለዓድ ሰዎች ኤፍሬምን መቱ።
5 ፤ ገለዓዳውያንም ኤፍሬም የሚያልፍበትን የዮርዳኖስን መሻገሪያ ያዙባቸው፤ የሸሸም የኤፍሬም ሰው። ልለፍ ባለ ጊዜ፥ የገለዓድ ሰዎች። አንተ ኤፍሬማዊ ነህን? አሉት፤ እርሱም። አይደለሁም ቢል፥
6 ፤ እነርሱ። አሁን ሺቦሌት በል አሉት፤ እርሱም አጥርቶ መናገር አልቻለምና። ሲቦሌት አለ፤ ይዘውም በዮርዳኖስ መሻገሪያ አረዱት፤ በዚያም ጊዜ ከኤፍሬም አርባ ሁለት ሺህ ሰዎች ወደቁ።
7 ፤ ዮፍታሔም በእስራኤል ላይ ስድስት ዓመት ፈረደ። ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ሞተ፥ ከገለዓድም ከተሞች በአንዲቱ ተቀበረ።
8 ፤ ከእርሱም በኋላ የቤተ ልሔሙ ኢብጻን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ።
9 ፤ ሠላሳም ወንዶች ልጆችና ሠላሳ ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ሠላሳ ሴቶች ልጆቹንም ወደ ውጭ አገር ዳረ፤ ለወንዶች ልጆቹም ከውጭ አገር ሴቶች ልጆችን አመጣ። በእስራኤልም ላይ ሰባት ዓመት ፈረደ።
10 ፤ ኢብጻንም ሞተ፥ በቤተ ልሔምም ተቀበረ።
11 ፤ ከእርሱም በኋላ ዛብሎናዊው ኤሎም በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ፤ እርሱም በእስራኤል ላይ አሥር ዓመት ፈረደ።
12 ፤ ዛብሎናዊውም ኤሎም ሞተ፥ በዛብሎንም ምድር ባለችው በኤሎም ተቀበረ።
13 ፤ ከእርሱም በኋላ የጲርዓቶናዊው የሂሌል ልጅ ዓብዶን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ።
14 ፤ አርባም ልጆች ሠላሳም የልጅ ልጆች ነበሩት፤ በሰባም አህያ ግልገሎች ላይ ይቀመጡ ነበር። በእስራኤልም ላይ ስምንት ዓመት ፈረደ።
15 ፤ የጲርዓቶናዊውም የሂሌል ልጅ ዓብዶን ሞተ፥ በተራራማውም በአማሌቃውያን ምድር በኤፍሬም ባለችው በጲርዓቶን ተቀበረ። a