ምዕራፍ 11

ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ጽኑዕ ኃያል ሰው የጋለሞታ ሴትም ልጅ ነበረ። ገለዓድም ዮፍታሔን ወለደ።
2 ፤ የገለዓድም ሚስት ወንዶች ልጆችን ወለደችለት፤ ልጆችዋም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን። የልዩ ሴት ልጅ ነህና በአባታችን ቤት አትወርስም ብለው አሳደዱት።
3 ፤ ዮፍታሔም ከወንድሞቹ ፊት ሸሽቶ በጦብ ምድር ተቀመጠ፤ ምናምንቴዎችም ሰዎች ተሰብስበው ዮፍታሔን ተከተሉት።
4 ፤ ከዚያም ወራት በኋላ የአሞን ልጆች ከእስራኤል ጋር ይዋጉ ነበር።
5 ፤ የአሞንም ልጆች ከእስራኤል ጋር በተዋጉ ጊዜ የገለዓድ ሽማግሌዎች ዮፍታሔን ከጦብ ምድር ለማምጣት ሄዱ።
6 ፤ ዮፍታሔንም። ና፥ ከአሞን ልጆች ጋር እንድንዋጋ አለቃችን ሁን አሉት።
7 ፤ ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች። የጠላችሁኝ ከአባቴም ቤት ያሳደዳችሁኝ እናንተ አይደላችሁምን? አሁን በተጨነቃችሁ ጊዜ ለምን ወደ እኔ መጣችሁ? አላቸው።
8 ፤ የገለዓድም ሽማግሌዎች ዮፍታሔን። ከእኛ ጋር እንድትወጣ፥ ከአሞንም ልጆች ጋር እንድትዋጋ፥ ስለዚህ አሁን ወደ አንተ ተመልሰን መጣን፤ በገለዓድም ሰዎች ሁሉ ላይ አለቃችን ትሆናለህ አሉት።
9 ፤ ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች። ከአሞን ልጆች ጋር ለመዋጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝ፥ እግዚአብሔርም በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው፥ እኔ አለቃችሁ እሆናለሁን? አላቸው።
10 ፤ የገለዓድም ሽማግሌዎች ዮፍታሔን። እግዚአብሔር በመካከላችን ምስክር ይሁን፤ በእርግጥ እንደ ቃልህ እናደርጋለን አሉት።
11 ፤ ዮፍታሔም ከገለዓድ ሽማግሌዎች ጋር ሄደ፥ ሕዝቡም በላያቸው ራስና አለቃ አደረጉት፤ ዮፍታሔም ቃሉን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በምጽጳ ተናገረ።
12 ፤ ዮፍታሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ። አገሬን ለመውጋት ወደ እኔ የምትመጣ አንተ ከእኔ ጋር ምን አለህ? ብሎ መልክተኞችን ላከ።
13 ፤ የአሞንም ልጆች ንጉሥ የዮፍታሔን መልክተኞች። እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ ከአርኖን ጀምሮ እስከ ያቦቅና እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ምድሬን ስለ ወሰደ ነው፤ አሁንም በሰላም መልሱልኝ ብሎ መለሰላቸው።
14 ፤ ዮፍታሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ መልክተኞችን እንደ ገና ላከ፥
15 ፤ እንዲህም አለው። ዮፍታሔ እንዲህ ይላል። እስራኤል የሞዓብን ምድር የአሞንንም ልጆች ምድር አልወሰደም፤
16 ፤ ነገር ግን ከግብፅ በወጣ ጊዜ፥ እስራኤልም በምድረ በዳ በኩል ወደ ኤርትራ ባሕር በሄደ ጊዜ፥ ወደ ቃዴስም በደረሰ ጊዜ፥
17 ፤ እስራኤል ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ። በምድርህ እንዳልፍ፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ ብሎ መልክተኞችን ላከ፤ የኤዶምያስም ንጉሥ አልሰማም። እንዲሁም ወደ ሞዓብ ንጉሥ ላከ፥ እርሱም አልፈቀደም።
18 ፤ እስራኤልም በቃዴስ ተቀመጠ። በምድረ በዳም በኩል ሄዱ፥ የኤዶምያስንና የሞዓብንም ምድር ዞሩ፤ ከሞዓብ ምድርም በምሥራቅ በኩል መጡ በአርኖንም ማዶ ሰፈሩ፤ አርኖንም የሞዓብ ድንበር ነበረና የሞዓብን ድንበር አላለፉም።
19 ፤ እስራኤልም ወደ አሞራዊው ወደ ሐሴቦን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልክተኞችን ላከ፤ እስራኤልም። በምድርህ በኩል ወደ ስፍራችን፥ እባክህ፥ አሳልፈን አለው።
20 ፤ ሴዎንም እስራኤል በድንበሩ እንዲያልፍ አላመነውም ነበር፤ ነገር ግን ሴዎን ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ በያሀጽም ሰፈረ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ።
21 ፤ የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ሴዎንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጠ፥ መቱአቸውም፤ እስራኤልም በዚያ ምድር ተቀምጠው የነበሩትን የአሞራውያንን ምድር ሁሉ ወረሰ።
22 ፤ ከአርኖንም እስከ ያቦቅ ድረስ ከምድረ በዳውም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ የአሞራውያንን ምድር ሁሉ ወረሱ።
23 ፤ የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሞራውያንን አስወገደ፤ አንተም ምድሩን ትወርሳለህን?
24 ፤ አምላክህ ካሞሽ የሚሰጥህን አትወርስምን? እኛም አምላካችን እግዚአብሔር ከፊታችን ያስወጣቸውን የእነርሱን ምድር እንወርሳለን።
25 ፤ ወይስ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ አንተ ትሻላለህን? በውኑ እርሱ እስራኤልን ከቶ ተጣላውን? ወይስ ተዋጋውን?
26 ፤ እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮችዋ፥ በአሮዔርና በመንደሮችዋ፥ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረ ጊዜ፥ በዚያ ዘመን ስለ ምን አልወሰዳችኋቸውም ነበር?
27 ፤ እኔ አልበደልሁህም፥ አንተ ግን ከእኔ ጋር እየተዋጋህ በድለኸኛል፤ ፈራጁ እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆችና በአሞን ልጆች መካከል ዛሬ ይፍረድ።
28 ፤ ነገር ግን ዮፍታሔ የላከበትን ቃል የአሞን ልጆች ንጉሥ አልሰማም።
29 ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በዮፍታሔ ላይ መጣ፤ እርሱም ገለዓድንና ምናሴን አለፈ፥ በገለዓድም ያለውን ምጽጳን አለፈ፥ ከምጽጳም ወደ አሞን ልጆች አለፈ።
30 ፤ ዮፍታሔም። በእውነት የአሞንን ልጆች በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፥
31 ፤ ከአሞን ልጆች ዘንድ በደኅና በተመለስሁ ጊዜ፥ ሊገናኘኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አቀርበዋለሁ ብሎ ለእግዚአብሔር ስእለት ተሳለ።
32 ፤ ዮፍታሔም ሊዋጋቸው ወደ አሞን ልጆች አለፈ፥ እግዚአብሔርም በእጁ አሳልፎ ሰጣቸው።
33 ፤ ከአሮዔርም እስከ ሚኒትና እስከ አቤልክራሚም ድረስ ሀያ ከተሞችን በታላቅ አገዳደል መታቸው። የአሞንም ልጆች በእስራኤል ልጆች ፊት ተዋረዱ።
34 ፤ ዮፍታሄም ወደ ቤቱ ወደ ምጽጳ መጣ፥ እነሆም ልጁ ከበሮ ይዛ እየዘፈነች ልትገናኘው ወጣች፤ ለእርሱም አንዲት ብቻ ነበረች፤ ከእርስዋም በቀር ወንድ ወይም ሴት ሌላ ልጅ አልነበረውም።
35 ፤ እርስዋንም ባየ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ። አወይ ልጄ ሆይ! ወደ እግዚአብሔር አፌን ከፍቻለሁና፥ ከዚያውም እመለስ ዘንድ አልችልምና በጣም አዋረድሽኝ አስጨነቅሽኝም አላት።
36 ፤ እርስዋም። አባቴ ሆይ፥ አፍህን ለእግዚአብሔር ከከፈትህ፥ እግዚአብሔር በጠላቶችህ በአሞን ልጆች ላይ ተበቅሎልሃልና በአፍህ እንደ ተናገርህ አድርግብኝ አለችው።
37 ፤ አባትዋንም። ይህ ነገር ይደረግልኝ፤ ከዚህ ሄጄ በተራሮች ላይ እንድወጣና እንድወርድ፥ ከባልንጀሮቼም ጋር ለድንግልናዬ እንዳለቅስ ሁለት ወር አሰናብተኝ አለችው።
38 ፤ እርሱም። ሂጂ አለ። ሁለት ወርም አሰናበታት፤ ከባልንጀሮችዋም ጋር ሄደች፥ በተራሮችም ላይ ለድንግልናዋ አለቀሰች።
39 ፤ ሁለትም ወር ከተፈጸመ በኋላ ወደ አባትዋ ተመለሰች፥ እንደ ተሳለውም ስእለት አደረገባት፤ እርስዋም ወንድ አላወቀችም ነበር።
40 ፤ የእስራኤልም ሴቶች ልጆች በዓመት በዓመቱ እየሄዱ የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በዓመት አራት ቀን ሙሾ እንዲያወጡ በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆነ።