ምዕራፍ 3

ከከነዓናውያንም ጋር መዋጋት ያላወቁትን እስራኤልን በእነርሱ፤
2 ፤ ይፈትናቸው ዘንድ፥ በፊትም ሰልፍን ያልለመዱ የእስራኤል ልጆች ትውልድ መዋጋትን ያውቁና ይማሩ ዘንድ እግዚአብሔር ያስቀራቸው አሕዛብ እነዚህ ናቸው፤
3 ፤ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ ከነዓናውያንም ሁሉ፥ ሲዶናውያንም፥ ከበኣልአርሞንዔም ተራራ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ በሊባኖስ ተራራ የሚኖሩትም ኤዊያውያን።
4 ፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ለአባቶቻቸው ያዘዘውን ትእዛዝ መስማታቸው እንዲታወቅ እስራኤል ይፈተኑባቸው ዘንድ እነዚህ ቀሩ።
5 ፤ የእስራኤልም ልጆች በከነዓናውያን በኬጢያውያንም በአሞራውያንም በፌርዛውያንም በኤዊያውያንም በኢያቡሳውያንም መካከል ተቀመጡ።
6 ፤ ሴት ልጆቻቸውንም አገቡአቸው፥ እነርሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻቸው ሰጡ፥ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ።
7 ፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር አደረጉ፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረስተው በኣሊምንና አስታሮትን አመለኩ።
8 ፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በመስጴጦምያ ንጉሥ በኵሰርሰቴም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የእስራኤልም ልጆች ለኵሰርሰቴም ስምንት ዓመት ተገዙለት።
9 ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም የሚያድናቸውን አዳኝ የካሌብን የታናሽ ወንድሙን የቄኔዝን ልጅ ጎቶንያልን አስነሣላቸው።
10 ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ መጣ፥ በእስራኤልም ላይ ይፈርድ ነበር፤ ለሰልፍ ወጣ፥ እግዚአብሔርም የመስጴጦምያን ንጉሥ ኵሰርሰቴምን በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እጁም በኵሰርሰቴም ላይ አሸነፈች።
11 ፤ ምድሪቱም አርባ ዓመት ዐረፈች፤ የቄኔዝም ልጅ ጎቶንያል ሞተ።
12 ፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር የሞዓብን ንጉሥ ዔግሎምን በእስራኤል ላይ አበረታባቸው።
13 ፤ የአሞንን ልጆችና አማሌቅን ወደ እርሱ ሰበሰበ፤ ሄዶም እስራኤልን መታ፥ ዘንባባም ያለባትን ከተማ ያዙአት።
14 ፤ የእስራኤልም ልጆች ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎም አሥራ ስምንት ዓመት ተገዙለት።
15 ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም ብንያማዊውን የጌራን ልጅ ናዖድን ግራኙን ሰው አዳኝ አስነሣላቸው፤ የእስራኤልም ልጆች በእርሱ እጅ ወደ ሞዓብ ንጉሥ ወደ ዔግሎም ግብር ላኩ።
16 ፤ ናዖድም ሁለት አፍ ያለው ርዝመቱ አንድ ክንድ የሆነ ሰይፍ አበጀ፥ ከልብሱም በታች በቀኝ ጭኑ በኩል አደረገው።
17 ፤ ለሞዓብም ንጉሥ ለዔግሎም ግብሩን አቀረበ፤ ዔግሎምም እጅግ ወፍራም ሰው ነበረ።
18 ፤ ግብሩንም ማቅረብ በጨረሰ ጊዜ፥ ግብር የተሸከሙትን ሰዎች ሰደደ።
19 ፤ ናዖድ ግን በጌልገላ ከነበሩት ትክል ድንጋዮች ዘንድ ተመልሶ። ንጉሥ ሆይ፥ የምሥጢር ነገር አለኝ አለ፤ ንጉሡም። ዝም በል አለ፤ በዙሪያውም የቆሙት ሁሉ ወጡ።
20 ፤ ናዖድም ወደ እርሱ ቀረበ፤ እርሱም በሰገነት ቤት ለብቻው ተቀምጦ ነበር። ናዖድም። የእግዚአብሔር መልእክት ለአንተ አለኝ አለ። ከዙፋኑም ተነሣ።
21 ፤ ናዖድም ግራ እጁን ዘርግቶ ከቀኝ ጭኑ ሰይፉን ወሰደ፥ ሆዱንም ወጋው፤
22 ፤ የሰይፉም እጀታው ደግሞ ከስለቱ በኋላ ገባ፤ ስቡም ስለቱን ከደነው፥ ሰይፉንም ከሆዱ መልሶ አላወጣውም፤ በኋላውም ወጣ።
23 ፤ ናዖድም ወደ ደርቡ ወጣ፥ የሰገነቱንም ደጅ ዘግቶ ቈለፈው።
24 ፤ ናዖድም ከሄደ በኋላ ባሪያዎቹ መጡ፤ የሰገነቱም ደጅ ተቈልፎ ባዩ ጊዜ። ምናልባት በሰገነቱ ውስጥ ወገቡን ይሞክር ይሆናል አሉ።
25 ፤ እስኪያፍሩም ድረስ እጅግ ዘገዩ፤ የሰገነቱንም ደጅ እንዳልከፈተ ባዩ ጊዜ መክፈቻውን ወስደው ከፈቱ፥ እነሆም፥ ጌታቸው በምድር ወድቆ ሞቶም አገኙት።
26 ፤ በዘገዩበትም ጊዜያት ናዖድ ሸሸ፥ ትክል ድንጋዮቹንም አለፈ፥ ወደ ቤይሮታም አመለጠ።
27 ፤ በመጣም ጊዜ በተራራማው በኤፍሬም አገር ቀንደ መለከት ነፋ፤ የእስራኤልም ልጆች ከእርሱ ጋር ከተራራማው አገር ወረዱ፥ እርሱም በፊታቸው ሄደ።
28 ፤ እርሱም። እግዚአብሔር ጠላቶቻችሁን ሞዓባውያንን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተከተሉኝ አላቸው። ተከትለውትም ወረዱ፥ ወደ ሞዓብም የሚያሻግረውን የዮርዳኖስን መሻገርያ ያዙ፥ ማንንም አላሳለፉም።
29 ፤ የዚያን ጊዜም ከሞዓብ አሥር ሺህ የሚያህሉትን፥ ጕልማሶችና ጽኑዓን ሁሉ፥ መቱ፤ አንድ እንኳ አላመለጠም።
30 ፤ በዚያም ቀን ሞዓብ ከእስራኤል እጅ በታች ተዋረደ፤ ምድሪቱም ሰማንያ ዓመት ዐረፈች።
31 ፤ ከእርሱም በኋላ የዓናት ልጅ ሰሜጋር ተነሣ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ስድስት መቶ ሰው በበሬ መውጊያ ገደለ፤ እርሱም ደግሞ እስራኤልን አዳነ።