ምዕራፍ 4

ናዖድም ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ።
2 ፤ እግዚአብሔርም በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቢስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ በአሕዛብ አሪሶት የተቀመጠው ሲሣራ ነበረ።
3 ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና፥ የእስራኤልንም ልጆች ሀያ ዓመት ያህል እጅግ ያስጨንቃቸው ነበር።
4 ፤ በዚያ ጊዜም ነቢይቱ የለፊዶት ሚስት ዲቦራ በእስራኤል ላይ ትፈርድ ነበረች።
5 ፤ እርስዋም በተራራማው በኤፍሬም አገር በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዛፍ ከሚባለው ከዘንባባው በታች ተቀምጣ ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እርስዋ ለፍርድ ይወጡ ነበር።
6 ፤ ልካም ከቃዴስ ንፍታሌም የአቢኒኤምን ልጅ ባርቅን ጠርታ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር። ሄደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ፥ ከአንተም ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን ልጆች አሥር ሺህ ሰዎች ውሰድ፤
7 ፤ እኔም የኢያቢስን ሠራዊት አለቃ ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሕዝቡንም ሁሉ ወደ አንተ ወደ ቂሶን ወንዝ እስባለሁ፥ በእጅህም አሳልፌ እሰጠዋለሁ ብሎ አላዘዘህምን? አለችው።
8 ፤ ባርቅም። አንቺ ከእኔ ጋር ብትሄጂ እኔ እሄዳለሁ፤ አንቺ ግን ከእኔ ጋር ባትሄጂ እኔ አልሄድም አላት።
9 ፤ እርሷም። በእውነት ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሲሣራን በሴት እጅ አሳልፎ ይሰጣልና በዚህ በምትሄድበት መንገድ ለአንተ ክብር አይሆንም አለችው። ዲቦራም ተነሥታ ከባርቅ ጋር ወደ ቃዴስ ሄደች።
10 ፤ ባርቅም ዛብሎንንና ንፍታሌምን ወደ ቃዴስ ጠራቸው፥ አሥር ሺህም ሰዎች ተከትለውት ወጡ፤ ዲቦራም ከእርሱ ጋር ወጣች።
11 ፤ ቄናዊውም ሔቤር ከሙሴ አማት ከኦባብ ልጆች ከቄናውያን ተለይቶ ድንኳኑን በቃዴስ አጠገብ በጻዕናይም እስከ ነበረው እስከ ትልቁ ዛፍ ድረስ ተከለ።
12 ፤ የአቢኒኤምም ልጅ ባርቅ ወደ ታቦር ተራራ እንደ ወጣ ለሲሣራ ነገሩት።
13 ፤ ሲሣራም ሰረገሎቹን ሁሉ፥ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች፥ ከእርሱም ጋር የነበሩትን ሕዝቡን ሁሉ ከአሪሶት ወደ ቂሶን ወንዝ ሰበሰባቸው።
14 ፤ ዲቦራም ባርቅን። እግዚአብሔር ሲሣራን በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥበት ቀን ዛሬ ነውና ተነሣ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር በፊትህ ወጥቶአል አለችው። ባርቅም አሥር ሺህ ሰዎች ተከትለውት ከታቦር ተራራ ወረደ።
15 ፤ እግዚአብሔርም ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው፤ ሲሣራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ።
16 ፤ ባርቅም ሰረገሎችንና ሠራዊቱን እስከ አሪሶት ድረስ አባረረ፤ የሲሣራም ሠራዊት ሁሉ በሰይፍ ስለት ወደቀ፤ አንድ እንኳ አልቀረም።
17 ፤ በአሶር ንጉሥም በኢያቢስና በቄናዊው በሔቤር ቤት መካከል ሰላም ነበረና ሲሣራ በእግሩ ሸሽቶ ወደ ቄናዊው ወደ ሔቤር ሚስት ወደ ኢያዔል ድንኳን ደረሰ።
18 ፤ ኢያዔልም ሲሣራን ለመገናኘት ወጥታ። ግባ፥ ጌታዬ ሆይ፥ ወደ እኔ ግባ፤ አትፍራ አለችው። ወደ እርስዋም ወደ ድንኳንዋ ገባ፥ በመጐናጸፊያዋም ሸፈነችው።
19 ፤ እርሱም። ጠምቶኛልና እባክሽ የምጠጣው ጥቂት ውኃ ስጭኝ አላት፤ እርስዋም የወተቱን አቁማዳ ፈትታ አጠጣችው፥ ሸፈነችውም።
20 ፤ እርሱም። ከድንኳኑ ደጃፍ ቁሚ፤ ሰውም መጥቶ። በዚህ ሰው አለን? ብሎ ቢጠይቅሽ አንቺ። የለም ትዪዋለሽ አላት።
21 ፤ የሔቤርም ሚስት ኢያዔል የድንኳን ካስማ ወሰደች፥ በእጅዋም መዶሻ ያዘች፥ ቀስ ብላም ወደ እርሱ ቀረበች፤ በጆሮግንዱ ካስማውን ቸነከረች፤ እርሱም ደክሞ እንቀላፍቶ ነበርና ካስማው ወደ መሬት ጠለቀ፥ እርሱም ሞተ።
22 ፤ እነሆም፥ ባርቅ ሲሣራን ሲያባርር ኢያዔል ልትገናኘው ወጥታ። ና የምትሻውንም ሰው አሳይሃለሁ አለችው። ወደ እርስዋም ገባ፥ እነሆም፥ ሲሣራን ወድቆ ሞቶም አገኘው፥ ካስማውም ከጆሮግንዱ ውስጥ ነበረ።
23 ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስን በእስራኤል ልጆች ፊት አዋረደ።
24 ፤ የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስንም እስኪያጠፉ ድረስ በከነዓን ንጉሥ በኢያቢስ ላይ የእስራኤል ልጆች እጅ እየበረታች ሄደች።