ምዕራፍ 17

በተራራማውም በኤፍሬም አገር ሚካ የተባለ አንድ ሰው ነበረ።
2 ፤ እናቱንም። ከአንቺ ዘንድ የተወሰደው፥ የረገምሽበትም፥ በጆሮዬም የተናገርሽበት አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር፥ እነሆ፥ በእኔ ዘንድ አለ፤ እኔም ወስጄዋለሁ አላት። እናቱም። ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ አለችው።
3 ፤ አንዱን ሺህ አንዱን መቶ ብርም መለሰላት፤ እናቱም። ይህን ብር የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል አድርጌ ከእጄ ስለ ልጄ ለእግዚአብሔር እቀድሰዋለሁ፤ አሁንም ለአንተ እመልሰዋለሁ አለች።
4 ፤ ለእናቱም ገንዘቡን በመለሰላት ጊዜ እናቱ ሁለቱን መቶ ብር ወስዳ ለአንጥረኛ ሰጠችው፥ እርሱም የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል አደረገው። ያም በሚካ ቤት ነበረ።
5 ፤ ሰውዮውም ሚካ የአምላክ ቤት ነበረው፤ ኤፉድና ተራፊም አደረገ፥ ከልጆቹም አንዱን ቀደሰው፥ ካህንም ሆነለት።
6 ፤ በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።
7 ፤ በቤተ ልሔም ይሁዳም ከይሁዳ ወገን የሆነ አንድ ጕልማሳ ነበረ፥ እርሱም ሌዋዊ ነበረ፥ በዚያም ይቀመጥ ነበር።
8 ፤ ይህም ሰው የሚቀመጥበትን ስፍራ ለመሻት ከከተማው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ወጣ፤ ሲሔድም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጣ።
9 ፤ ሚካም። ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም። ከቤተ ልሔም ይሁዳ የሆንሁ ሌዋዊ ነኝ፤ የምቀመጥበትንም ስፍራ ለመሻት እሄዳለሁ አለው።
10 ፤ ሚካም። ከእኔ ዘንድ ተቀመጥ፥ አባትና ካህንም ሁነኝ፤ እኔም ልብሶችንና ምግብህን፥ በእየዓመቱም አሥር ብር እሰጥሃለሁ አለው። ሌዋዊውም ገባ።
11 ፤ ሌዋዊውም ከሰውዮው ጋር መቀመጥን ፈቀደ፤ ጕልማሳውም ከልጆቹ እንደ አንዱ ሆነለት።
12 ፤ ሚካም ሌዋዊውን ቀደሰ፥ ጕልማሳውም ካህኑ ሆነለት፥ በሚካም ቤት ነበረ።
13 ፤ ሚካም። ሌዋዊ ካህን ስለ ሆነልኝ እግዚአብሔር መልካም እንዲሠራልኝ አሁን አውቃለሁ አለ።