ምዕራፍ 13

የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን እጅ አርባ ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው።
2 ፤ ከዳን ወገን የሆነ ማኑሄ የሚባል አንድ የጾርዓ ሰው ነበረ፤ ሚስቱም መካን ነበረች፥ ልጅም አልወለደችም።
3 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት። እነሆ፥ አንቺ መካን ነሽ፥ ልጅም አልወለድሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ።
4 ፤ አሁንም ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅን የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ።
5 ፤ እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ እርሱም እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል።
6 ፤ ሴቲቱም ወደ ባልዋ መጥታ። አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፥ መልኩም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እጅግ የሚያስደነግጥ ነበረ፤ ከወዴትም እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፥ እርሱም ስሙን አልነገረኝም።
7 ፤ እርሱም። እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና አሁን የወይን ጠጅ የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ አለኝ ብላ ተናገረች።
8 ፤ ማኑሄም። ጌታ ሆይ፥ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው፥ እባክህ፥ እንደ ገና ወደ እኛ ይምጣ፤ ለሚወለደውም ልጅ ምን እንድናደርግ ያስገንዝበን ብሎ ወደ እግዚአብሔር ለመነ።
9 ፤ እግዚአብሔርም የማኑሄን ድምፅ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና ለሴቲቱ በእርሻ ውስጥ ተቀምጣ ሳለች ተገለጠላት፤ ባልዋ ማኑሄ ግን ከእርስዋ ጋር አልነበረም።
10 ፤ ሴቲቱም ፈጥና ሮጠች ለባልዋም። እነሆ፥ በቀደም ዕለት ወደ እኔ የመጣው ሰው ደግሞ ተገለጠልኝ ብላ ነገረችው።
11 ፤ ማኑሄም ተነሥቶ ሚስቱን ተከተለ፥ ወደ ሰውዮውም መጥቶ። ከዚህች ሴት ጋር የተነጋገርህ አንተ ነህን? አለው። እርሱም። እኔ ነኝ አለ።
12 ፤ ማኑሄም። ቃልህ በደረሰ ጊዜ የልጁ ሥርዓት ምንድር ነው? የምናደርግለትስ ምንድር ነው? አለው።
13 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን። ሴቲቱ ከነገርኋፅት ሁሉ ትጠንቀቅ።
14 ፤ ከወይንም ከሚወጣው ሁሉ አትብላ፥ የወይን ጠጅንም የሚያሰክርንም ነገር አትጠጣ፥ ርኩስም ነገር ሁሉ አትብላ፤ ያዘዝኋትን ሁሉ ትጠብቅ አለው።
15 ፤ ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ። የፍየል ጠቦት እስክናዘጋጅልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ቆይ አለው።
16 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን። አንተ የግድ ብትለኝ መብልህን አልበላም፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማዘጋጀት ብትወድድ ለእግዚአብሔር አቅርበው አለው። ማኑሄም የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር።
17 ፤ ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ። ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው? አለው።
18 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ። ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃለህ? አለው።
19 ፤ ማኑሄም የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቍርባን ወስዶ በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቀረበው። መልአኩም ተአምራት አደረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር።
20 ፤ ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔርም መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ዐረገ፤ ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፥ በምድርም በግምባራቸው ተደፉ።
21 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ዳግመኛ ላማኑሄና ለሚስቱ አልተገለጠም፤ ያን ጊዜም ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አወቀ።
22 ፤ ማኑሄም ሚስቱን። እግዚአብሔርን አይተናልና ሞት እንሞታለን አላት።
23 ፤ ሚስቱም። እግዚአብሔርስ ሊገድለን ቢወድድ ኖሮ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ከእጃችን ባልተቀበለን፥ ይህንም ነገር ሁሉ ባላሳየን፥ እንዲህ ያለ ነገርም በዚህ ጊዜ ባላስታወቀን ነበር አለችው።
24 ፤ ሴቲቱም ወንድ ልጅ ወለደች፥ ስሙንም ሶምሶን ብላ ጠራችው፤ ልጁም አደገ እግዚአብሔርም ባረከው።
25 ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ውስጥ ሊያነቃቃው ጀመረ።