ምዕራፍ 14

ሶምሶንም ወደ ተምና ወረደ፥ በተምናም ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አየ።
2 ፤ ወጥቶም ለአባቱና ለእናቱ። በተምና ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አይቻለሁ፤ አሁንም እርስዋን አጋቡኝ አላቸው።
3 ፤ አባቱና እናቱም። ካልተገረዙት ከፍልስጥኤማውያን ሚስት ለማግባት ትሄድ ዘንድ ከወንድሞችህ ሴቶች ልጆች ከሕዝቤም ሁሉ መካከል ሴት የለምን? አሉት። ሶምሶንም አባቱን። ለዓይኔ እጅግ ደስ አሰኝታኛለችና እርስዋን አጋባኝ አለው።
4 ፤ እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን ላይ ምክንያት ይፈልግ ነበርና ነገሩ ከእርሱ ሆነ፤ አባቱና እናቱ ግን አላወቁም። በዚያን ጊዜም ፍልስጥኤማውያን በእስራኤል ላይ ገዦች ነበሩ።
5 ፤ ሶምሶንም አባቱና እናቱም ወደ ተምና ወረዱ፥ በተምናም ወዳለው ወደ ወይኑ ስፍራ መጡ፤ እነሆም፥ የአንበሳ ደቦል እያገሣ ወደ እርሱ ደረሰ።
6 ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ በኃይል ወረደ፤ ጠቦትን እንደሚቆራርጥ በእጁ ምንም ሳይኖር ቈራረጠው፤ ያደረገውንም ለአባቱና ለእናቱ አልነገረም።
7 ፤ ወርዶም ከሴቲቱ ጋር ተነጋገረ፤ እጅግም ደስ አሰኘችው።
8 ፤ ከጥቂትም ቀን በኋላ ሊያገባት ተመለሰ፥ የአንበሳውንም ሬሳ ያይ ዘንድ ከመንገድ ፈቀቅ አለ፤ እነሆም፥ በአንበሳው ሬሳ ውስጥ ንብ ሰፍሮበት ነበር፥ ማርም ነበረበት።
9 ፤ በእጁም ወስዶ መንገድ ለመንገድ እየበላ ሄደ፤ ወደ አባቱና ወደ እናቱ መጣ፥ ማሩንም ሰጣቸው፥ እነርሱም በሉ፤ ማሩንም ከአንበሳው ሬሳ ውስጥ እንደ ወሰደ አልነገራቸውም።
10 ፤ አባቱም ወደ ሴቲቱ ወረደ፤ ጎበዞችም እንዲህ ያደርጉ ነበርና ሶምሶን በዚያ በዓል አደረገ።
11 ፤ ባዩትም ጊዜ ከእርሱ ጋር ይሆኑ ዘንድ ሌሎች ሠላሳ ሰዎች ሰጡት።
12 ፤ ሶምሶንም። እንቆቅልሽ ልስጣችሁ፤ በሰባቱም በበዓሉ ቀኖች ውስጥ ፈትታችሁ ብትነግሩኝ፥ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ እሰጣችኋለሁ፤
13 ፤ መፍታትም ባትችሉ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ ትሰጡኛላችሁ አላቸው። እነርሱም። እንድንሰማው እንቆቅልሽህን ንገረን አሉት።
14 ፤ እርሱም። ከበላተኛው ውስጥ መብል ወጣ፥ ከብርቱም ውስጥ ጥፍጥ ወጣ አላቸው። ሦስት ቀንም እንቈቅልሹን መተርጎም አልቻሉም።
15 ፤ በአራተኛውም ቀን የሶምሶንን ሚስት። እንቈቅልሹን እንዲነግረን ባልሽን ሸንግዪው፥ አለዚያም እንቺንና የአባትሽን ቤት በእሳት እናቃጥላለን፤ ወደዚህ ጠራችሁን ልትገፉን ነውን? አሉአት።
16 ፤ የሶምሶንም ሚስት በፊቱ እያለቀሰች። በእውነት ጠልተኸኛል፥ ከቶም አትወድደኝም፤ ለሕዝቤ ልጆች እንቈቅልሽ ሰጥተሃቸዋልና ትርጓሜውንም አልነገርኸኝም አለችው። እርሱም። እነሆ፥ ለአባቴና ለእናቴ አልነገርኋቸውም፥ ለአንቺ እነግርሻለሁን? አላት።
17 ፤ ሰባቱንም የበዓል ቀን በፊቱ አለቀሰች፤ እርስዋም ነዝንዛዋለችና በሰባተኛው ቀን ነገራት። ትርጓሜውንም ለሕዝብዋ ልጆች ነገረች።
18 ፤ በሰባተኛውም ቀን ፀሐይ ሳትገባ የከተማይቱ ሰዎች። ከማር የሚጣፍጥ ምንድር ነው? ከአንበሳስ የሚበረታ ማን ነው? አሉት። እርሱም። በጥጃዬ ባላረሳችሁ የእንቈቅልሼን ትርጓሜ ባላወቃችሁ ነበር አላቸው።
19 ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ በኃይል ወረደ፤ ወደ አስቀሎናም ወረደ፥ ከዚያም ሠላሳ ሰዎችን ገደለ፥ ልብሳቸውንም ወስዶ እንቈቅልሹን ለፈቱት ሰዎች ሰጠ። ቍጣውም ነደደ፥ ወደ አባቱም ቤት ወጣ።
20 ፤ የሶምሶን ሚስት ግን ከተባበሩት ከሚዜዎቹ ለአንደኛው ሆነች። a