ምዕራፍ 15

ከዚህ ነገር በኋላም የእግዚአብሔር ቃል በራእይ ወደ አብራም መጣ፥ እንዲህ ሲል። አብራም ሆይ፥ አትፍራ፤ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው።
2 ፤ አብራምም። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ ምንን ትሰጠኛለህ? እኔም ያለ ልጅ እሄዳለሁ፤ የቤቴም መጋቢ የደማስቆ ሰው ይህ ኤሊዔዘር ነው አለ።
3 ፤ አብራምም። ለእኔ ዘር አልሰጠኸኝም፤ እነሆም፥ በቤቴ የተወለደ ሰው ይወርሰኛል አለ።
4 ፤ እነሆም፥ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት። ይህ አይወርስህም፤ ነገር ግን ከጉልበትህ የሚወጣው ይወርስሃል።
5 ፤ ወደ ሜዳም አወጣውና። ወደ ሰማይ ተመልከት፥ ከዋክብትንም ልትቈጥራቸው ትችል እንደ ሆነ ቍጠር አለው። ዘርህም እንደዚሁ ይሆናል አለው።
6 ፤ አብራምም በእግዚአብሔር አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት።
7 ፤ ይህችን ምድር ትወርሳት ዘንድ እንድሰጥህ ከከለዳውያን ዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ አለው።
8 ፤ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንድወርሳት በምን አውቃለሁ? አለ።
9 ፤ እርሱም። የሦስት ዓመት ጊደር፥ የሦስት ዓመት ፍየልም፥ የሦስት ዓመት በግም፥ ዋኖስም፥ ርግብም ያዝልኝ አለው።
10 ፤ እነዚህንም ሁሉ ወሰደለት፥ በየሁለትም ከፈላቸው፥ የተከፈሉትንም በየወገኑ ትይዩ አደረጋቸው፤ ወፎችን ግን አልከፈለም።
11 ፤ አሞራዎችም በሥጋው ላይ ወረዱ፥ አብራምም አበረራቸው።
12 ፤ ፀሐይም በገባች ጊዜ በአብራም ከባድ እንቅልፍ መጣበት፤ እነሆም፥ ድንጋጤና ታላቅ ጨለማ ወደቀበት፤
13 ፤ አብራምንም አለው። ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በእርግጥ እወቅ፤ ባሪያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል።
14 ፤ ደግሞም በባርነት በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርዳለሁ፤ ከዚያም በኋላ በብዙ ከብት ይወጣሉ። q2 ኤሊዔዘር የተባለውን የግዕዙን መጽሐፍ ኢያውብር ይለዋል።
15 ፤ አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ።
16 ፤ በአራተኛው ትውልድ ግን ወደዚህ ይመለሳሉ፤ የአሞራውያን ኃጢአት ገና አልተፈጸመምና።
17 ፤ ፀሐይም በገባች ጊዜ ታላቅ ጨለማ ሆነ፤ የምድጃ ጢስና የእሳት ነበልባል በዚያ በተከፈለው መካከል አለፈ።
18 ፤ በዚያ ቀን እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን አደረገ። ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ትልቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ይህችን ምድር ለዘርህ ሰጥቼአለሁ፤
19 ፤ ቄናውያንን ቄኔዛውያንንም
20 ፤ ቀድሞናውያንንም ኬጢያውያንንም
21 ፤ ፌርዛውያንንም ራፋይምንም አሞራውያንንም ከነዓናውያንንም ጌርጌሳውያንንም ኢያቡሳውያንንም።