ምዕራፍ 5

የአዳም የትውልዱ መጽሐፍ ይህ ነው። እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤
2 ፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፥ ባረካቸውም። ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው።
3 ፤ አዳምም ሁለት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ልጅንም በምሳሌው እንደ መልኩ ወለደ፤ ስሙንም ሴት ብሎ ጠራው።
4 ፤ አዳምም ሴትን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
5 ፤ አዳምም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ሠላሳ ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
6 ፤ ሴትም ሁለት መቶ አምስት ዓመት ኖረ፥ ሄኖስንም ወለደ፤
7 ፤ ሴትም ሄኖስን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ሰባት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
8 ፤ ሴትም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አሥራ ሁለት ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
9 ፤ ሄኖስም መቶ ዘጠና ዓመት ኖረ፥ ቃይናንንም ወለደ፤
10 ፤ ሄኖስም ቃይናንን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ አሥራ አምስት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
11 ፤ ሄኖስም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አምስት ዓመት ሆነ ሞተም።
12 ፤ ቃይናንም መቶ ሰባ ዓመት ኖረ፥ መላልኤልንም ወለደ፤
13 ፤ ቃይናንም መላልኤልን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ አርባ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
14 ፤ ቃይናንም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አሥር ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
15 ፤ መላልኤልም መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ያሬድንም ወለደ፤
16 ፤ መላልኤልም ያሬድን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ሠላሳ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
17 ፤ መላልኤልም የኖረበት ዘመን ሁሉ ስምንት መቶ ዘጠና አምስት ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
18 ፤ ያሬድም መቶ ስድሳ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ሄኖክንም ወለደ
19 ፤ ያሬድም ሄኖክን ከወለደ በኋላ የኖረው ስምንት መቶ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
20 ፤ ያሬድም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ሁለት ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
21 ፤ ሄኖክም መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ማቱሳላንም ወለደ፤
22 ፤ ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፤ ማቱሳላንም ከወለደ በኋላ የኖረው ሁለት መቶ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
23 ፤ ሄኖክም የኖረበት ዘመን ሁሉ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሆነ።
24 ፤ ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፤ እግዚአብሔር ወስዶታልና።
25 ፤ ማቱሳላም መቶ ሰማኒያ ሰባት ዓመት ኖረ፥ ላሜሕንም ወለደ፤
26 ፤ ማቱሳላም ላሜሕን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
27 ፤ ማቱሳላም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ዘጠኝ ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
28 ፤ ላሜሕም መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ልጅንም ወለደ።
29 ፤ ስሙንም። እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ይህ ያሳርፈናል ሲል ኖኅ ብሎ ጠራው።
30 ፤ ላሜሕም ኖኅን ከወለደ በኋላ የኖረው አምስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ።
31 ፤ ላሜሕ የኖረበት ዘመን ሁሉ ሰባት መቶ አርባ ሰባት ዓመት ሆነ፤ ሞተም።
32 ፤ ኖኅም የአምስት መቶ ዓመት ሰው ነበረ፤ ኖኅም ሴምን ካምን ያፌትንም ወለደ።