ምዕራፍ 39

ዮሴፍ ግን ወደ ግብፅ ወረደ፤ የፈርዖን ጃንደረባ የዘበኞቹም አለቃ የሚሆን የግብፅ ሰው ጲጥፋራ ወደ ግብፅ ካወረዱት ከእስማኤላውያን እጅ ገዛው።
2 ፤ እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበረ፥ ሥራውም የተከናወነለት ሰው ሆነ፤ በግብፃዊው ጌታውም ቤት ነበረ።
3 ፤ ጌታውም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለ፥ እርሱ የሚሠራውንም ሁሉ እግዚአብሔር በእጁ እንዲያከናውንለት አየ።
4 ፤ ዮሴፍም በጌታው ፊት ሞገስን አገኘ፥ እርሱንም ያገለግለው ነበር፤ በቤቱም ላይ ሾመው፥ ያለውንም ሁሉ በእጁ ሰጠው።
5 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በቤቱ ባለውም ሁሉ ላይ ከሾመው በኋላ እግዚአብሔር የግብፃዊውን ቤት ስለ ዮሴፍ ባረከው፤ የእግዚአብሔር በረከት በውጪም በግቢም ባለው ሁሉ ላይ ሆነ።
6 ፤ ያለውንም ሁሉ ለዮሴፍ አስረከበ፤ ከሚበላውም እንጀራ በቀር ምንም የሚያውቀው አልነበረም። የዮሴፍም ፊቱ መልከ መልካምና ውብ ነበረ።
7 ፤ ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይንዋን ጣለች። ከእኔም ጋር ተኛ አለችው።
8 ፤ እርሱም እንቢ አለ፥ ለጌታውም ሚስት እንዲህ አላት። እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ምንም ምን የሚያውቀው የለም፥ ያለውንም ሁሉ ለእኔ አስረክቦኛል፤
9 ፤ ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለ ሆንሽ ከአንቺም በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?
10 ፤ ይህንም ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር ይተኛ ዘንድ ከእርስዋም ጋር ይሆን ዘንድ አልሰማትም።
11 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በዚያን ጊዜ ሥራውን እንዲሠራ፤ ወደ ቤቱ ገባ፤ በቤትም ውስጥ ከቤት ሰዎች ማንም አልነበረም።
12 ፤ ከእኔ ጋር ተኛ ስትል ልብሱን ተጠማጥማ ያዘች፤ እርሱም ልብሱን በእጅዋ ትቶላት ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ።
13 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ልብሱን ትቶ ወደ ውጭ እንደ ሸሸ ባየች ጊዜ፥
14 ፤ የቤትዋን ሰዎች ወደ እርስዋ ጠርታ እንዲህ ብላ ነገረቻቸው። እዩ፤ ዕብራዊው ሰው በእኛ እንዲሣለቅ አግብቶብናል፤፤ እርሱ ከእኔ ጋር ሊተኛ ወደ እኔ ገባ፥ እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ ጮኽሁ፤
15 ፤ ድምፄንም ከፍ አድርጌ እንደ ጮኽሁ ቢሰማ ልብሱን በእኔ ዘንድ ጥሎ ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ።
16 ፤ ጌታው ወደ ቤቱ እስኪገባ ድረስም ልብሱን ከእርስዋ ዘንድ አኖረች።
17 ፤ ይህንም ነገር እንዲህ ብላ ነገረችው። ያገባህልን ዕብራዊው ባሪያ ሊሣለቅብኝ ወደ እኔ ገባ፤
18 ፤ እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ልብሱን በእጄ ተወና ወደ ውጭ ሸሸ።
19 ፤ ጌታውም። ባሪያህ እንዲህ አደረገኝ ብላ የነገረችውን የሚስቱን ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ።
20 ፤ የዮሴፍም ጌታ ወሰደው፥ የንጉሡ እስረኞችም ወደሚታሰሩበት ስፍራ ወደ ግዞት ቤት አገባው፤ ከዚያም በግዞት ነበረ።
21 ፤ እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበረ ምሕረትንም አበዛለት፥ በግዞት ቤቱም አለቃ ፊት ሞገስን ሰጠው።
22 ፤ የግዞት ቤቱም አለቃ በግዞት ያሉትን እስረኞች ሁሉ በዮሴፍ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዚያም የሚደረገው ነገር ሁሉ እርሱ የሚያደርገው ነበረ።
23 ፤ የግዞት ቤቱም አለቃ በእጁ ያለውን ነገር ከቶ አላሰበም፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ የሚያደርገውንም ሁሉ እግዚአብሔር ያቀናለት ነበር።