ምዕራፍ 22

ከእነዚህም ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፥ እንዲህም አለው። አብርሃም ሆይ። አብርሃምም። እነሆ፥ አለሁ አለ።
2 ፤ የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ።
3 ፤ አብርሃምም በማለዳ ተነሥቶ አህያውን ጫነ፥ ሁለቱንም ሎሌዎቹንና ልጁን ይስሕቅን ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ እንጨትንም ለመሥዋዕት ሰነጠቀ፤ ተነሥቶም እግዚአብሔር ወዳለው ቦታ ሄደ።
4 ፤ በሦስተኛውም ቀን አብርሃም ዓይኑን አነሣና ቦታውን ከሩቅ አየ።
5 ፤ አብርሃምም ሎሌዎቹን አላቸው። አህያውን ይዛችሁ ከዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ሄደን እንሰግዳለን፥ ወደ እናንተም እንመለሳለን።
6 ፤ አብርሃምም የመሥዋዕቱን እንጨት አንሥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸከመው፤ እርሱም እሳቱንና ቢላዋውን በእጁ ያዘ፥ ሁለቱም አብረው ሄዱ።
7 ፤ ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን ተናገረው። አባቴ ሆይ አለ። እርሱም። እነሆኝ፥ ልጄ አለው። እሳቱና እንጨቱ ይኸው አለ፤ የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት ነው? አለ።
8 ፤ አብርሃምም። ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል አለው፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ።
9 ፤ እግዚአብሔር ወዳለውም ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያውን ሠራ፥ እንጨትንም ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው በእንጨቱ ላይ አጋደመው።
10 ፤ አብርሃምም እጁን ዘረጋ፥ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣ።
11 ፤ የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና። አብርሃም አብርሃም አለው፤
12 ፤ እርሱም። እነሆኝ አለ። እርሱም። በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ።
13 ፤ አብርሃምም ዓይኑን አነሣ፥ በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄደ በጉንም ወሰደው፥ በልጁም ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው።
14 ፤ አብርሃምም ያንን ቦታ ያህዌ ይርኤ ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእግዚአብሔር ተራራ ይታያል ይባላል።
15 ፤ የእግዚአብሔር መልአክም አብርሃምን ከሰማይ ሁለተኛ ጊዜ ጠራው፥
16 ፤ እንዲህም አለው። እግዚአብሔር። በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፥ አንድ ልጅህንም አልከለከልህምና
17 ፤ በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፥ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤
18 ፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፥ ቃሌን ሰምተሃልና።
19 ፤ አብርሃምም ወደ ብላቴኖቹ ተመለሰ፥ ተነሥተውም ወደ ቤርሳቤህ አብረው ሄዱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ ተቀመጠ።
20 ፤ ይህም ከሆነ በኋልላ ለአብርሃም እንዲህ ተብሎ ተነገረ። እነሆ፥ ሚልካ ደግሞ ለወንድምህ ለናኮር ልጆችን ወለደች፤
21 ፤ እነርሱም በኵሩ ዑፅ፥ ወንድሙ ቡዝ፥ የአራም አባት ቀሙኤል፥
22 ፤ ኮዛት፥ ሐዞ፥ ፊልዳሥ፥ የድላፍ፥ ባቱኤል ናቸው።
23 ፤ ባቱኤልም ርብቃን ወለደ፤ እነዚህን ስምንቱን ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር ወለደች።
24 ፤ ሬሕማ የሚሉአት ቁባቱ ደግሞ ጥባህን፥ ገአምን፥ ተሐሸን፥ ሞክሳን ወለደች።