ምዕራፍ 49

ያዕቆብም ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አለ። በኋለኛው ዘመን የሚያገኛችሁን እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ።
2 ፤ እናንት የያዕቆብ ልጆች ተሰብሰቡ፥ ስሙም፤ አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ።
3 ፤ ሮቤል፥ አንተ በኵር ልጄና ኃይሌ፥ የጕብዝናዬም መጀመሪያ ነህ፤ የክብር አለቃና የኃይል አለቃ።
4 ፤ እንደ ውኃ የምትዋልል ነህ፤ አለቅነት ለአንተ አይሁን፤ ወደ አባትህ መኝታ ወጥተሃልና፤ አረከስኸውም፤ ወደ አልጋዬም ወጣ።
5 ፤ ስምዖንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፤ ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው።
6 ፤ በምክራቸው፥ ነፍሴ፥ አትግባ፤ ከጉባኤአቸውም ጋር፥ ክብሬ፥ አትተባበር፤ በቍጣቸው ሰውን ገድለዋልና፥ በገዛ ፈቃዳቸውም በሬን አስነክሰዋልና።
7 ፤ ቍጣቸው ርጉም ይሁን፥ ጽኑ ነበርና፤ ኵርፍታቸውም፥ ብርቱ ነበርና፤ በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ፥ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ።
8 ፤ ይሁዳ፥ ወንድሞችህ አንተን ያመሰግኑሃል፤ እጅህ በጠላቶችህ ደንደስ ላይ ነው፤ የአባትህ ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ።
9 ፤ ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው፤ ልጄ ሆይ፥ ከአደንህ ወጣህ፤ እንደ አንበሳ አሸመቀ፥ እንደ ሴት አንበሳም አደባ፤ ያስነሣውስ ዘንድ ማን ይችላል?
10 ፤ በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፥ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፥ ገዥ የሆነው እስኪመጣ ድረስ፤ የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል።
11 ፤ ውርንጫውን በወይን ግንድ ያስራል፥ የአህያይቱንም ግልገል በወይን አረግ፤ ልብሱን በወይን ያጥባል፥ መጎናጸፊያውንም በወይን ደም።
12 ፤ ዓይኑም ከወይን ይቀላል፤ ጥርሱም ከወተት ነጭ ይሆናል።
13 ፤ ዛብሎን በባሕር ዳር ይቀመጣል፤ እርሱም ለመርከቦች ወደብ ይሆናል፤ ዳርቻውም እስከ ሲዶና ድረስ ነው።
14 ፤ ይሳኮር አጥንተ ብርቱ አህያ ነው፥ በበጎች ጕረኖም መካከል ያርፋል።
15 ፤ ዕረፍትም መልካም መሆንዋን አየ፥ ምድሪቱም የለማች መሆንዋን፤ ትከሻውን ለመሸከም ዝቅ አደረገ፥ በሥራም ገበሬ ሆነ።
16 ፤ ዳን በወገኑ ይፈርዳል፥ ከእስራኤል ነገድ እንደ አንዱ።
17 ፤ ዳን በጐዳና ላይ እንደ እባብ ይሆናል፥ በመንገድም እንደ ቀንዳም እባብ፤ ፈረሱን ከሰኮናው ይነክሳል፥ ፈረሰኛም ወደ ኋላው ይወድቃል።
18 ፤ እግዚአብሔር ሆይ፥ መድኃኒትህን እጠብቃለሁ።
19 ፤ ጋድን ዘማቾች ይዘምቱበታል፤ እርሱ ግን ተከታትሎ ይዘምትባቸዋል።
20 ፤ የአሴር እንጀራው ወፍራም ነው፥ ለነገሥታቱም ደስ የሚያሰኝ መብልን ይሰጣል።
21 ፤ ንፍታሌም የተፈታ ሚዳቋ ነው፤ መልካም ቃልን ይሰጣል።
22 ፤ ዮሴፍ ትንሹ የፍሬ ዛፍ ነው፥ በምንጭ አጠገብ የሚያፈራ የፍሬ ዛፍ፤ አረጎቹ በቅጥር ላይ ያድጋሉ።
23 ፤ ቀስተኞች አስቸገሩት፥ ነደፉትም፥ ተቃወሙትም፤
24 ፤ ነገር ግን ቀስቱ እንደ ጸና ቀረ፤ የእጆቹም ክንድ በያዕቆብ አምላክ እጅ በረታ፥ በዚያው በጠባቂው በእስራኤል ዓምድ፥
25 ፤ በአባትህ አምላክ እርሱም የሚረዳህ፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ እርሱም የሚባርክህ፥ በሰማይ በረከት ከላይ በሚገኝ፥ በጥልቅም በረከት ከታች በሚሠራጭ፥ በጡትና በማኅፀን በረከት።
26 ፤ የአባትህ በረከቶች ጽኑዓን ከሆኑ ከተራሮች በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፤ ዘላለማውያን ከሆኑ ከኮረፍቶችም በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፤ እነርሱም በዮሴፍ ራስ ላይ ይሆናሉ፥ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነው ራስ አናት ላይ።
27 ፤ ብንያም ነጣቂ ተኵላ ነው፤ የበዘበዘውን በጥዋት ይበላል፥ የማረከውንም በማታ ይካፈላል።
28 ፤ እነዚህም ሁሉ አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው፤ አባታቸው የነገራቸው ይህ ነው፥ ባረካቸውም፤ እያንዳንዳቸውን እንደ በረከታቸው ባረካቸው።
29 ፤ እንዲህ ብሎም አዘዛቸው። እኔ ወደ ወገኖቼ እሰበሰባለሁ፤ በኬጢያዊ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ጋር ቅበሩኝ፤
30 ፤ እርስዋም በከነዓን ምድር በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊ ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት፥ ባለ ድርብ ክፍል ዋሻ ናት።
31 ፤ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ከዚያ ተቀበሩ፤ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ከዚያ ተቀበሩ፤ ከዚያም እኔ ልያን ቀበርኋት፤
32 ፤ እርሻውና በእርስዋ ላይ ያለችው ዋሻ ከኬጢ ልጆች የተገዙ ናቸው።
33 ፤ ያዕቆብም ትእዛዙን ለልጆቹ ተናግሮ በፈጸመ ጊዜ እግሮቹን በአልጋው ላይ ሰብስቦ ሞተ፥ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ።