ምዕራፍ 30

ራሔልም ለያዕቆብ ልጆችን እንዳልወለደች ባየች ጊዜ በእኅትዋ ቀናችባት፤ ያቆብንም። ልጅ ስጠኝ፤ ይህስ ካልሆነ እሞታለሁ አለችው።
2 ፤ ያዕቆብም ራሔልን ተቆጥቶ። በውኑ እኔ የሆድን ፍሬ በነሣሽ በእግዚአብሔር ቦታ ነኝን? አላት።
3 ፤ እርስዋም ባሪያዬ ባላ እነሆ አለች፤ ድረስባት፤ በእኔም ጭን ላይ ትውለድ፥ የእርስዋም ልጆች ለእኔ ደግሞ ይሁኑልኝ አለች።
4 ፤ ባሪያዋን ባላንም ሚስት ትሆነው ዘንድ ለእርሱ ሰጠችው፤ ያዕቆብም ደረሰባት።
5 ፤ ባላም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደችለት።
6 ፤ ራሔልም። እግዚአብሔር ፈረደልኝ፥ ቃሌንም ደግሞ ሰማ፥ ወንድ ልጅንም ሰጠኝ አለች፤ ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ ጠራችው።
7 ፤ የራሔልም ባሪያ ባላ ደግማ ፀነሰች፥ ለያዕቆብም ሁለተኛ ወንድ ልጅን ወለደች።
8 ፤ ራሔልም። ብርቱ ትግልን ከእኅቴ ጋር ታገልሁ፥ አሸነፍሁም አለች፤ ስሙንም ንፍታሌም ብላ ጠራችው።
9 ፤ ልያም መውለድን እንዳቆመች ባየች ጊዜ ባሪያዋን ዘለፋን ወሰደች፥ ሚስት ትሆነውም ዘንድ ለያዕቆብ ሰጠችው።
10 ፤ የልያ ባሪያ ዘለፋም ወንድ ልጅን ለያዕቆብ ወለደች።
11 ፤ ልያም። ጉድ አለች፤ ስሙንም ጋድ ብላ ጠራችው።
12 ፤ የልያ ባሪያ ዘለፋም ዳግመኛ ለያዕቆብ ወንድ ልጅን ወለደች።
13 ፤ ልያም። ደስታ ሆነልኝ፤ ሴቶች ያመሰግኑኛልና አለች፤ ስሙንም አሴር ብላ ጠራችው።
14 ፤ ሮቤል ስንዴ በሚታጨድበት ወራት ወጣ፥ በእርሻም እንኮይ አገኘ፥ ለእናቱ ለልያም አመጣላት። ራሔልም ልያን። የልጅሽን እንኮይ ስጪኝ አለቻት።
15 ፤ እርስዋም። ባሌን መውሰድሽ በውኑ ጥቂት ነገር ነውን? አሁን ደግሞ የልጄን እንኮይ ልትወስጂ ትፈልጊያለሽን? አለቻት። ራሔልም። እንኪያስ ስለ ልጅሽ እንኮይ በዚህች ሌሊት ከአንቺ ጋር ይተኛ አለች።
16 ፤ ያዕቆብም ሲመሽ ከዱር ገባ፥ ልያም ልትቀበለው ወጣች እንዲህም አለችው። ወደ እኔ ትገባለህ፤ በልጄ እንኮይ በእርግጥ ተከራይቼሃለሁና። በዚያችም ሌሊት ከእርስዋ ጋር ተኛ።
17 ፤ እግዚአብሔርም የልያን ጸሎት ሰማ፥ ፀነሰችም፥ አምስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች።
18 ፤ ልያም። ባሪያዬን ለባሌ ስለ ሰጠሁ እግዚአብሔር ዋጋዬን ሰጠኝ አለች፤ ስሙንም ይሳኮር ብላ ጠራችው።
19 ፤ ልያም ደግማ ፀነሰች፥ ስድስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች።
20 ፤ ልያም። እግዚአብሔር መልካም ስጦታን ሰጠኝ፤ እንግዲህስ ባሌ ከእኔ ጋር ይኖራል፥ ስድስት ልጆችን ወልጄለታለሁና አለች፤ ስሙንም ዛብሎን ብላ ጠራችው።
21 ፤ ከዚያም በኋላ ሴት ልጅን ወለደች፥ ስምዋንም ዲና አለቻት።
22 ፤ እግዚአብሔርም ራሔልን አሰበ፥ እግዚአብሔርም ተለመናት፥ ማኅፀንዋንም ከፈተላት፤
23 ፤ ፀነሰችም፥ ወንድ ልጅንም ወለደችና። እግዚአብሔር ስድቤን አስወገደ አለች፤
24 ፤ ስሙንም። እግዚአብሔር ሁለተኛ ወንድ ልጅን ይጨምርልኝ ስትል ዮሴፍ ብላ ጠራችው።
25 ፤ ራሔልም ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው። ወደ ስፍራዬ ወደ አገሬም እመለስ ዘንድ አሰናብተኝ።
26 ፤ ስለ እነርሱ የተገዛሁላቸውን ሚስቶቼንና ልጆቼን ስጠኝና ልሂድ፤ የተገዛሁልህን መገዛት ታውቃለህና።
27 ፤ ላባም። በዓይንህ ፊት ሞገስን የማገኝ ብሆንስ ከዚሁ ተቀመጥ፤ እግዚአብሔር በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ ተመልክቼአለሁና አለው።
28 ፤ ደመወዝህን ንገረኝ፥ እርሱንም እሰጥሃለሁ አለ።
29 ፤ እርሱም አለው። እንዴት እንዳገለገልሁህ፥ ከብትህንም እንዴት እንደ ጠበቅሁልህ አንተ ታውቃለህ።
30 ፤ ከእኔ መምጣት በፊት የነበረህ ጥቂት ነበርና፥ ዛሬም እጅግ በዛ፤ ወደ አንተ በመምጣቴም እግዚአብሔር ባረክህ፤ አሁንም እኔ ደግሞ ለቤቴ የምሠራው መቼ ነው?
31 ፤ እርሱም። የምሰጥህ ምንድር ነው? አለ። ያዕቆብም አለው። ምንም አትስጠኝ፤ ይህንም ነገር ብታደርግልኝ እንደ ገና በጎችህን አበላለሁ እጠብቃለሁም።
32 ፤ ዛሬ በመንጎችህ በኩል አልፋለሁ፥ በዚያም ከበጎችህ መካከል ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለበቱን ጥቁሩንም በግ ሁሉ፥ ከፍየሎቹም ነቍጣና ዝንጕርጕር ያለበቱን እለያለሁ፤ እነርሱም ደመወዜ ይሆናሉ።
33 ፤ ስለዚህም በፊትህ ያለውን ደመወዜን ለመመልከት በመጣህ ጊዜ ወደ ፊት ጻድቅነቴ ይመሰክርልኛል፤ ከፍየሎች ዝንጕርጕርና ነቍጣ የሌለበት ከበግ ጠቦቶችም ጥቁር ያልሆኑ ሁሉ፥ እርሱ በእኔ ዘንድ ቢገኝ እንደ ተሰረቀ ይቆጠርብኝ።
34 ፤ ላባም። እነሆ እንደ ቃልህ ይሁን አለ።
35 ፤ በዚያም ቀን ከተባቶቹ ፍየሎች ሽመልመሌ መሳይና ነቍጣ ያለባቸውን፥ ከእንስቶቹም ፍየሎች ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለባቸውን፥ ነጭ ያለበትን ማንኛውንም ሁሉ፥ ከበጎቹም መካከል ጥቁሩን በግ ሁሉ ለይቶ ለልጆቹ ሰጣቸው።
36 ፤ በእርሱና በያዕቆብ መካከልም የሦስት ቀን መንገድ ያህል አራቃቸው፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን በጎች ይጠብቅ ነበር።
37 ፤ ያዕቆብም ልብን ለውዝ ኤርሞን ከሚባሉ እንጨቶች እርጥብ በትርን ወስዶ በበትሮቹ ውስጥ ያለው ነጭ እንዲታይ ነጭ ሽመልመሌ አድርጎ ላጣቸው።
38 ፤ የላጣቸውንም በትሮች በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ በበጎቹ ፊት አኖራቸው፤ በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ ይጎመጁ ነበር።
39 ፤ በጎቹም በትሮቹን አይተው ከመጎምጀታቸው የተነሣ ፀነሱ፤ በጎቹም ሽመልመሌ መሳይና ዝንጕርጕር ነቍጣም ያለበቱን ወለዱ።
40 ፤ ያዕቆብም ጠቦቶቹን ለየ፥ ሽመልመሌ መሳይና ጥቁር ያለባቸውን በጎቹንም ሁሉ በላባ በጎች ፊት ለፊት አኖረ፤ መንጎቹንም ለብቻቸው አቆማቸው፥ ወደ ላባም በጎች አልጨመራቸውም።
41 ፤ እንዲህም ሆነ፤ የበረቱት በጎች በጎመጁ ጊዜ፥ በጎቹ በትሮቹን አይተው በበትሮቹ አምሳል ይፀንሱ ዘንድ ያዕቆብ በትሮቹን በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ ከበጎቹ ፊት አደረገ፤
42 ፤ በደከሙ በጎችም ፊት በትሩን አያደርገውም ነበር፤ የደከሙትም ለላባ፥ የበረቱትም ለያዕቆብ ሆኑ።
43 ፤ ያ ሰውም እጅግ ባለ ጠጋ ሆነ፤ ብዙም ከብት ሴቶችም ወንዶችም ባሪያዎች ግመሎችም አህዮችም ሆኑለት።