ምዕራፍ 24

አብርሃምም ሸመገለ በዘመኑም አረጀ፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሥራው ሁሉ ባረከው።
2 ፤ አብርሃምም ሎሌውን የቤቱን ሽማግሌ የከብቱን ሁሉ አዛዥ አለው።
3 ፤ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ እኔም አብሬ ከምኖራቸው ከከነዓን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስት እንዳትወስድለት በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ፤
4 ፤ ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ተወላጆቼ ትሄዳለህ፥ ለልጄ ለይስሐቅም ሚስትን ትወስድለታለህ።
5 ፤ ሎሌውም። ሴቲቱ ምናልባት ወደዚህ አገር ከእኔ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደ ሆነ ልጅህን ወደ ወጣህበት አገር ልመልሰውን? አለው።
6 ፤ አብርሃምም አለው። ልጄን ወደዚያ እንዳትመልስ ተጠንቀቅ፤
7 ፤ ከአባቴ ቤት ከተወለድሁባት ምድርም ያወጣኝ። ይህችንም ምድር እሰጥሃለሁ ብሎ የነገረኝና የማለልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ መልአኩን በፊትህ ይሰድዳል፥ ከዚያም ለልጄ ሚስትን ትወስዳለህ።
8 ፤ ሴቲቱም ከአንተ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደ ሆነ ከዚህ ካቀረብሁህ መሐላ ንጹሕ ነህ፤ ልጄን ግን ወደዚያ አትመልሰው።
9 ፤ ሎሌውም ከጌታው ከአብርሃም ጭን በታች እጁን አደረገ ስለዚሁም ነገር ማለለት።
10 ፤ ሎሌውም ከጌታው ግመሎች መካከል አሥር ግመሎችን ወስዶ፥ ከጌታውም ዕቃ መልካም መልካሙን ይዞ ተነሣ፤ ተነሥቶም ወደ መስጼጦምያ ወደ ናኮር ከተማ ሄደ።
11 ፤ ሲመሽም ሴቶች ውኃ ሊቀዱ በሚወጡበት ጊዜ ከከተማይቱ ውጪ በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ግመሎቹን አስበረከከ።
12 ፤ እንዲህም አለ። የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፥ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ።
13 ፤ እነሆ፥ በዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ፥ የዚህችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃውን ሊቀዱ ይመጣሉ፤
14 ፤ ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዪ የምላት እርስዋም። አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ፥ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ።
15 ፤ ይህን መናገሩንም ሳይፈጽም እነሆ፥ ሚልካ የወለደችው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በጫንቃዋ ተሸክማ ወጣች፤ ሚልካም የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት ናት።
16 ፤ ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች፤ ወደ ምንጭም ወረደች እንስራዋንም ሞላች፥ ተመልሳም ወጣች።
17 ፤ ሎሌውም ሊገናኛት ሮጠና። ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ ታጠጪኝ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት።
18 ፤ እርስዋም። ጌታዬ ሆይ፥ ጠጣ አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን በእጅዋ አውርዳ አጠጣችው።
19 ፤ እርሱንም ካጠጣች በኋላ። ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ አለች።
20 ፤ ፈጥናም ውኃውን ከእንስራዋ በማጠጫው ውስጥ ገለበጠችው፥ ደግሞም ልትቀዳ ወደ ጕድጓዱ ሮጠች፥ ለግመሎቹም ሁሉ ውኃ ቀዳች።
21 ፤ ሰውዮውም ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር፤ እግዚአብሔር መንገዱን አቅንቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅም ዝም አለ።
22 ፤ ግመሎቹም ከጠጡ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ሰውዮው ግማሽ ሰቅል የሚመዘን የወርቅ ቀለበት፥ ለእጆችዋም አሥር ሰቅል የሚመዘን ጥንድ የወርቅ አምባር አወጣ፤
23 ፤ እንዲህም አላት። አንቺ የማን ልጅ ነሽ? እስኪ ንገሪኝ፤ በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኛልን?
24 ፤ አለችውም። እኔ ሚልካ ለናኮር የወለደችው የባቱኤል ልጅ ነኝ።
25 ፤ በእኛ ዘንድ ገለባና ገፈራ የሚበቃ ያህል አለ፥ ለማደሪያም ደግሞ ስፍራ አለን።
26 ፤ ሰውዮውም አጎነበሰ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገደ ።
27 ፤ እንዲህም አለ። ቸርነቱንና እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እኔ በመንገድ ሳለሁ እግዚአብሔር ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ።
28 ፤ ብላቴናይቱም ሮጠች፥ ለእናትዋም ቤት ይህን ነገር ሁሉ ተናገረች።
29 ፤ ለርብቃም ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ ላባም ወደ ውጪ ወደ ውኃው ምንጭ ወደ ሰውዮው ሮጠ።
30 ፤ ቀለበቱንና አምባሮቹን በእኅቱ እጅ ባየ ጊዜ፥ የእኅቱን የርብቃንም ነገር። ያ ሰው እንዲህ አለኝ ያለችውን በሰማ ጊዜ፥ እርሱ ወደዚያ ሰው መጣ፤ እነሆም፥ በውኃው ምንጭ አጠገብ ከግመሎቹ ዘንድ ቆሞ ነበር።
31 ፤ እርሱም አለው። አንተ የእግዚአብሔር ቡሩክ፥ ግባ፤ ስለምን አንተ በውጪ ቆመሃል? እኔም ቤቱን ለግመሎችህም ስፍራ አዘጋጅቼአለሁ።
32 ፤ ሰውዮውም ወደ ቤት ገባ፥ ግመሎቹንም አራገፈ፤ ገለባና ገፈራም ለግመሎቹ አቀረበ፤ እግሩን ይታጠብ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ላሉት ሰዎች እግር ውኃ አቀረበ።
33 ፤ መብልንም በፊቱ አቀረበለት፤ እርሱ ግን። ነገሬን እስክናገር ድረስ አልበላም አለ። እርሱም። ተናገር አለው።
34 ፤ እርሱም አለ። እኔ የአብርሃም ሎሌ ነኝ።
35 ፤ እግዚአብሔርም ጌታዬን እጅግ ባረከው፥ አገነነውም፤ በጎችንና ላሞችን፥ ብርንም፥ ወርቅንም፥ ወንዶች ባሪያዎችንና ሴቶች ባሪያዎችን፥ ግመሎችንም አህዮችንም ሰጠው።
36 ፤ ሣራም የጌታዬ ሚስት በእርጅናው ለጌታዬ ወንድ ልጅን ወለደች፤ የነበረውንም ሁሉ ሰጠው።
37 ፤ ጌታዬም እንዲህ ሲል አማለኝ። እኔ ካለሁበት አገር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስትን አትውሰድ
38 ፤ ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት ወደ ወገኔም ሂድ፥ ለልጄም ሚስትን ውሰድለት።
39 ፤ ጌታዬንም። ሴቲቱ ምናልባት ባትከተለኝሳ? አልሁት።
40 ፤ እርሱም አለኝ። አካሄዴን በፊቱ ያደረግሁለት እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፥ መንገድህንም ያቀናል። ለልጄም ከወገኖቼ ከአባቴም ቤት ሚስትን ትወስዳለህ፤
41 ፤ የዚያን ጊዜ ከመሐላዬ ንጹሕ ነህ፤ ወደ ዘመዶቼ ሄደህ እነርሱ ባይሰጡህ ካማልሁህ መሐላ ንጹሕ ትሆናለህ።
42 ፤ ዛሬም ወደ ውኃው ምንጭ መጣሁ፥ እንዲህም አልሁ። የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዛሬ የምሄድበትን መንገዴን ብታቀናልኝ፤
43 ፤ እነሆ፥ እኔ በውኃው ምንጭ ላይ ቆሜአለሁ፤ ውኃ ልትቀዳ ለምትመጣውም ቆንጆ። ጥቂት ውኃ ከእንስራሽ አጠጪኝ ስላት፥
44 ፤ እርስዋም። አንተ ጠጣ፥ ደግሞም ለግመሎችህ እቀዳለሁ የምትለኝ፥ እግዚአብሔር ለጌታዬ ልጅ ያዘጋጃት ሴት እርስዋ ትሁን።
45 ፤ እኔም የልቤን መናገር ገና ሳልፈጽም፥ እነሆ፥ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ወጣች፥ ወደ ምንጭም ወርዳ ውኃ ቀዳች፤ እኔም። እስኪ አጠጪኝ አልኋት።
46 ፤ ፈጥናም እንስራዋን ከጫንቃዋ አወረደችና። አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህንም ደግሞ አጠጣለሁ አለች፤ እኔም ጠጣሁ፥ ግመሎቼንም ደግሞ አጠጣች።
47 ፤ እኔም። አንቺ የማን ልጅ ነሽ? ብዬ ጠየቅኋት። እርስዋም። ሚልካ ለናኮር የወለደችለት የባቱኤል ልጅ ነኝ አለች፤ ቀለበትም አደረግሁላት፥ ለእጆችዋም አምባሮች አደረግሁላት።
48 ፤ በግምባሬም አጎነበስሁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገድሁ፤ የጌታዬን የወንድሙን ልጅ ለልጁ እወስድ ዘንድ በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ።
49 ፤ አሁንም ቸርነትና እውነት ለጌታዬ ትሠሩ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ ይህም ባይሆን ንገሩኝ፥ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ እል ዘንድ።
50 ፤ ላባና ባቱኤልም መለሱ እንዲህም አሉ። ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶአል ክፉም በጎም ልንመልስልህ አንችልም።
51 ፤ ርብቃ እንኋት በፊትህ ናት፤ ይዘሃት ሂድ፥ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለጌታህም ልጅ ሚስት ትሁን።
52 ፤ የአብርሃምም ሎሌ ነገራቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ምድር ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ።
53 ፤ ሎሌውም የብርና የወርቅ ጌጥ ልብስም አወጣ፥ ለርብቃም ሰጣት፤ የከበረ ስጦታንም ለወንድምዋና ለእናትዋ አቀረበ።
54 ፤ እርሱም ከእርሱም ጋር ያሉት በሉ ጠጡም፥ ከዚያም አደሩ፤ ማልደውም ተነሡና። ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው ።
55 ፤ ወንድምዋና እናትዋም። ብላቴናይቱ አንድ አሥር ቀን ያህል እንኳ ከእኛ ዘንድ ትቀመጥ፤ ከዚያም በኋላ ትሄዳለች አሉ።
56 ፤ እርሱም። እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው።
57 ፤ እነርሱም። ብላቴናይቱን እንጥራና ከአፍዋ እንጠይቅ አሉ።
58 ፤ ርብቃንም ጠርተው። ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን? አሉአት። እርስዋም። እሄዳለሁ አለች።
59 ፤ እኅታቸውንም ርብቃን ሞግዚትዋንም የአብርሃምን ሎሌና ሰዎቹንም አሰናበቱአቸው።
60 ፤ ርብቃንም መረቁአትና። አንቺ እኅታችን፥ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽም የጠላቶችን ደጅ ይውረስ አሉአት።
61 ፤ ርብቃም ተነሣች ደንገጥሮችዋም፥ በግመሎችም ላይ ተቀምጠው ያንን ሰው ተከተሉት፤ ሎሌውም ርብቃን ተቀብሎ ሄደ።
62 ፤ ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ በሚሉአት ምንጭ መንገድ መጣ፤ በአዜብ ምድር ተቀምጦ ነበርና።
63 ፤ ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር፤ ዓይኖቹንም አቀና፥ እነሆም ግመሎች ሲመጡ አየ።
64 ፤ ርብቃም ዓይኖችዋን አቀናች፥ ይስሐቅንም አየች፥ ከግመልም ወረደች።
65 ፤ ሎሌውንም። ሊገናኘን በሜዳ የሚመጣ ይህ ሰው ማን ነው? አለችው። ሎሌውም። እርሱ ጌታዬ ነው አላት፤ እርስዋም መሸፈኛ ወስዳ ተከናነበች።
66 ፤ ሎሌውም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው።
67 ፤ ይስሐቅም ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን አገባት፥ ርብቃንም ወሰዳት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወደዳትም፤ ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና። a