ምዕራፍ 2

ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ።
2 ፤ እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ።
3 ፤ እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና።
4 ፤ እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን ባደረገ አምላክ ሰማይንና ምድርን ቀን፥ በተፈጠሩ ጊዜ የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው።
5 ፤ የሜዳ ቁጥቋጦ ሁሉ በምድር ላይ ገና አልነበረም፤ የሜዳውም ቡቃያ ሁሉ ገና አልበቀለም ነበር፤ እግዚአብሔር አምላክ ምድር ላይ አላዘነበም ነበርና፥ ምድርንም የሚሠራባት ሰው አልነበረም፤
6 ፤ ነገር ግን ጉም ከምድር ትወጣ ነበር፥ የምድርንም ፊት ሁሉ ታጠጣ ነበር።
7 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።
8 ፤ እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው።
9 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ።
10 ፤ ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፤ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር።
11 ፤ የአንደኛው ወንዝ ስም ፊሶን ነው፤ እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የኤውላጥ ምድርን ይከብባል፤ የዚያም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፤
12 ፤ ከዚያም ሉልና የከበረ ድንጋይ ይገኛል።
13 ፤ የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።
14 ፤ የሦስተኛውም ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው፤ እርሱም በአሦር ምሥራቅ የሚሄድ ነው።
15 ፤ አራተኛውም ወንዝ ኤፍራጥስ ነው። እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው።
16 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው። ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤
17 ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።
18 ፤ እግዚአብሔር አምላክም አለ። ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።
19 ፤ እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረገ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ።
20 ፤ አዳምም ለእንስሳት ሁሉ፥ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣላቸው፤ ነገር ግን ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር።
21 ፤ እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው።
22 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት።
23 ፤ አዳምም አለ። ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።
24 ፤ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።
25 ፤ አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፥ አይተፋፈሩም ነበር።