ምዕራፍ 48

ከዚህም ነገር በኋላ እንዲህ ሆነ፤ እነሆ አባትህ ታምሞአል ብለው ለዮሴፍ ነገሩት፤ እርሱም ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ።
2 ፤ ለያዕቆብም። እነሆ ልጅህ ዮሴፍ መጥቶልሃል ብለው ነገሩት፤ እስራኤልም ተጠነካከረ፥ በአልጋውም ላይ ተቀመጠ።
3 ፤ ያዕቆብ ዮሴፍን አለው። ሁሉን የሚችል አምላክ በከነዓን ምድር በሎዛ ተገለጠልኝ፥ ባረከኝም
4 ፤ እንዲህም አለኝ። እነሆ ፍሬያማ አደርግሃለሁ፥ አበዛሃለሁም፥ ለብዙም ሕዝብ ጉባኤ አደርግሃለሁ፤ ይህችንም ምድር ከአንተ በኋላ ለዘላለም ርስት ለዘርህ እሰጣታለሁ።
5 ፤ አሁንም እኔ ወደ አንተ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ ምድር የተወለዱልህ ሁለቱ ልጆችህ ለእኔ ይሁኑ፤ ኤፍሬምና ምናሴ ለእኔ እንደ ሮቤልና እንደ ስምዖን ናቸው።
6 ፤ ከእነርሱም በኋላ የምትወልዳቸው ልጆች ለአንተ ይሁኑ፤ በርስታቸው በወንድሞቻቸው ስም ይጠሩ።
7 ፤ እኔም ከመስጴጦምያ በመጣሁ ጊዜ፥ ወደ ኤፍራታ ለመግባት ጥቂት ቀርቶኝ በመንገድ ሳለሁ፥ ራሔል በከነዓን ምድር ሞተችብኝ፤ በዚያም በኤፍራታ መንገድ ላይ፥ እርስዋም ቤተ ልሔም ናት፥ ቀበርኋት።
8 ፤ እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች አይቶ። እነዚህ እነማን ናቸው? አለው።
9 ፤ ዮሴፍም ለአባቱ። እግዚአብሔር በዚህ የሰጠኝ ልጆቼ ናቸው አለ። እርሱም። እባርካቸው ዘንድ ወደዚህ አቅርብልኝ አለ።
10 ፤ የእስራኤልም ዓይኖች ከሽምግልና የተነሣ ከብደው ነበር፥ ማየትም አይችልም ነበር፤ ወደ እርሱም አቀረባቸው፥ ሳማቸውም፥ አቀፋቸውም።
11 ፤ እስራኤልም ዮሴፍን። ፊትህን አያለሁ ብዬ አላሰብሁም ነበር፤ እነሆም እግዚአብሔር ዘርህን ደግሞ አሳየኝ አለው።
12 ፤ ዮሴፍም ከጕልበቱ ፈቀቅ አደረጋቸው፥ ወደ ምድርም በግምባሩ ሰገደ።
13 ፤ ዮሴፍም ሁለቱን ልጆቹን ወሰደ፥ ኤፍሬምንም በቀኙ በእስራኤል ግራ፥ ምናሴንም በግራው በእስራኤል ቀኝ አደረገው፥ ወደ እርሱም አቀረባቸው።
14 ፤ እስራኤልም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረው፥ እርሱም ታናሽ ነበረ፥ ግራውንም በምናሴ ራስ ላይ አኖረ፤ እጆቹንም አስተላለፈ፥ ምናሴ በኵር ነበርና።
15 ፤ ያዕቆብም ዮሴፍን ባረከ እንዲህም አለ። አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥
16 ፤ ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፤ ስሜም የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ ይጠራ፤ በምድርም መካከል ይብዙ።
17 ፤ ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ጭኖ ባየ ጊዜ አሳዘነው፤ የአባቱንም እጅ በምናሴ ራስ ላይ ይጭነው ዘንድ ከኤፍሬም ራስ ላይ አነሣው።
18 ፤ ዮሴፍም አባቱን። አባቴ ሆይ እንዲህ አይደለም፥ በኵሩ ይህ ነውና፤ ቀኝህን በራሱ ላይ አድርግ አለው።
19 ፤ አባቱም እንቢ አለ እንዲህ ሲል። አወቅሁ ልጄ ሆይ፥ አወቅሁ፤ ይህም ደግሞ ሕዝብ ይሆናል ታላቅም ይሆናል፤ ነገር ግን ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፥ ዘሩም የአሕዛብ ሙላት ይሆናል።
20 ፤ በዚያም ቀን እንዲህ ብሎ ባረካቸው። በእናንተ እስራኤል እንዲህ ብሎ ይባርካል። እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርግህ። ኤፍሬምንም ከምናሴ ፊት አደረገው።
21 ፤ እስራኤልም ዮሴፍን። እነሆ እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል፥ ወደ አባቶቻችሁም ምድር ይመልሳችኋል፤
22 ፤ እኔም ከአሞራውያን በሰይፌና በቀስቴ የወሰድሁትን ለአንተ ከወንድሞችህ አንድ እጅ አብልጬ ሰጠሁህ አለው።