ምዕራፍ 29

ያዕቆብም ተነሥቶ ወደ ምሥራቅ ሰዎች አገር ሄደ።
2 ፤ በሜዳውም እነሆ ጕድጓድን አየ፥ በዚያም ሦስት የበጎች መንጎች በላዩ ተመስገው ነበር፤ ከዚያ ጕድጓድ በጎቹን ያጠጡ ነበርና፤ በጕድጓዱም አፍ የነበረው ድንጋይ ትልቅ ነበረ።
3 ፤ መንጎችም ሁሉ ከዚያ በተከማቹ ጊዜ ድንጋዩን ከጕድጓዱ አፍ ገለል አድርገው በጎቹን ያጠጡ ነበር፤ ድንጋዩንም ወደ ስፍራው መልሰው በጕድጓዱ አፍ እንደ ገና ይገጥሙት ነበር።
4 ፤ ያዕቆብም። ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንት የወዴት ናችሁ? አላቸው። እነርሱም። እኛ የካራን ነን አሉት።
5 ፤ የናኮርን ልጅ ላባን ታውቁታላችሁን? አላቸው። እነርሱም። እናውቀዋለን አሉት።
6 ፤ እርሱ። ደኅና ነውን? አላቸው። እነርሱም። አዎን ደኅና ነው፤ አሁንም ልጁ ራሔል ከበጎች ጋር መጣች አሉት።
7 ፤ እርሱም። ቀኑ ገና ቀትር ነው፥ ከብቶቹ የሚከማቹበት ሰዓቱም ገና አልደረሰም፤ አሁንም በጎቹን አጠጡና ሄዳችሁ አሰማሩአቸው አላቸው።
8 ፤ እነርሱም አሉ። መንጎች ሁሉ እስኪከማቹና ድንጋዩን ከጕድጓዱ አፍ እስኪገለብጡት ድረስ አንችልም፤ ከዚያም በኋላ በጎቹን እናጠጣለን።
9 ፤ እርሱም ገና ከእነርሱ ጋር ሲነጋገር እነሆ የላባ ልጅ ራሔል ከአባትዋ በጎች ጋር ደረሰች፤ እርስዋ የአባትዋን በጎች ትጠብቅ ነበርና።
10 ፤ ያዕቆብም የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልንና የእጎቱን የላባን በጎች ባየ ጊዜ፥ ቀረበ ከጕድጓዱም አፍ ድንጋዩን ገለበጠ፥ የአጎቱን የላባን በጎችንም አጠጣ።
11 ፤ ያዕቆብም ራሔልን ሳማት፥ ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ።
12 ፤ ያዕቆብም የአባትዋ ዘመድና የርብቃ ልጅ መሆኑን ለራሔል አስታወቃት፤ እርስዋም ሮጣ ሄዳ ለአባትዋ ይህን ነገር ነገረችው።
13 ፤ ላባም የእኅቱን ልጅ የያዕቆብን ወሬ በሰማ ጊዜ ሊቀበለው ሮጠ፥ አቅፎም ሳመው፥ ወደ ቤቱም አገባው። ነገሩንም ሁሉ ለላባ ነገረው ።
14 ፤ ላባም። በእውነት አንተ አጥንቴ ሥጋዬም ነህ አለው። አንድ ወር የሚያህልም ከእርሱ ጋር ተቀመጠ።
15 ፤ ላባም ያዕቆብን። ወንድሜ ስለሆንህ በከንቱ ታገለግለኛለህን? ምንዳህ ምንድር ነው? ንገረኝ አለው።
16 ፤ ለላባም ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ስም ራሔል ነበረ።
17 ፤ ልያም ዓይነ ልም ነበረች፤ ራሔል ግን መልከ መልካም ነበረች ፊትዋም ውብ ነበረ።
18 ፤ ያዕቆብም ራሔልን ወደደ፤ እንዲህም አለ። ስለ ታናሺቱ ልጅህ ስለ ራሔል ሰባት ዓመት እገዛልሃለሁ።
19 ፤ ላባም። ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለአንተ ብሰጣት ይሻላል፤ ከእኔ ጋር ተቀመጥ አለ።
20 ፤ ያዕቆብም ስለ ራሔል ሰባት ዓመት ተገዛ፤ እርስዋንም ይወድዳት ስለነበረ በእርሱ ዘንድ እንደ ጥቂት ቀን ሆነለት።
21 ፤ ያዕቆብም ላባን። ወደ እርስዋ እገባ ዘንድ ሚስቴን ስጠኝ፥ ቀኔ ተፈጽሞአልና አለው።
22 ፤ ላባም የዚያን ስፍራ ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፥ ሰርግም አደረገ።
23 ፤ በመሸም ጊዜ ልጁን ልያን ወስዶ ለያዕቆብ አገባለት፤ ያዕቆብም ወደ እርስዋ ገባ።
24 ፤ ላባም ለልጁ ለልያ ባሪያይቱን ዘለፋን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት።
25 ፤ በነጋም ጊዜ እነሆ ልያ ሆና ተገኘች፤ ላባንም። ምነው እንደዚህ አደረግህብኝ? ያገለገልሁህ ስለ ራሔል አልነበረምን? ለምን አታለልኸኝ? አለው።
26 ፤ ላባም እንዲህ አለ። በአገራችን ታላቂቱ ሳለች፥ ታናሺቱን እንሰጥ ዘንድ ወግ አይደለም፤
27 ፤ ይህችንም ሳምንት ፈጽም፤ ሌላ ሰባት ዓመት ደግሞ እኔን ስለምታገለግለኝ አገልግሎት እርስዋን ደግሞ እሰጥሃለሁ።
28 ፤ ያዕቆብም እንዲህ አደረገ፥ ይህችንም ሳምንት ፈጸመ፤ ልጁን ራሔልንም ለእርሱ ሚስት ትሆን ዘንድ ሰጠው።
29 ፤ ላባም ለልጁ ለራሔል ባርያይቱን ባላን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት ።
30 ፤ ያዕቆብም ወደ ራሔል ደግሞ ገባ። ራሔልንም ከልያ ይልቅ ወደዳት፤ ሌላ ሰባት ዓመትም ተገዛለት።
31 ፤ እግዚአብሔርም ልያ የተጠላች መሆንዋን ባየ ጊዜ ማኅፀንዋን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች።
32 ፤ ልያም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፥ ስሙንም ሮቤል ብላ ጠራችው፤ እግዚአብሔር መከራዬን አይቶአልና፥ እንግዲህም ወዲህ ባሌ ይወድደኛል ብላለችና።
33 ፤ ደግሞም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ እኔ እንደ ተጠላሁ እግዚአብሔር ስለ ሰማ ይህን ደገመኝ አለች፤ ስሙንም ስምዖን ብላ ጠራችው።
34 ፤ ደግሞም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ አሁንም ባሌ ወደ እኔ ይጠጋል፥ ሦስት ወንዶች ልጆችን ወልጄለታለሁና አለች፤ ስለዚህም ስሙን ሌዊ ብላ ጠራችው።
35 ፤ ደግሞም ፀነስች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ አለች፤ ስለዚህም ስሙን ይሁዳ ብላ ጠራችው። መውለድንም አቆመች።