ምዕራፍ 8

እግዚአብሔርም ኖኅን፥ በመርከብም ከእርሱ ጋር የነበረውን አራዊቱን ሁሉ፥ እንስሳውንም ሁሉ አሰበ፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ነፋስን አሳለፈ፥ ውኃውም ጎደለ፤
2 ፤ የቀላዩም ምንጮች የሰማይም መስኮቶች ተደፈኑ፥ ዝናብም ከሰማይ ተከለከለ፤
3 ፤ ውኃውም ከምድር ላይ እያደር እያደር ቀለለ፥ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጎደለ።
4 ፤ መርከቢቱም በሰባተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች ላይ ተቀመጠች።
5 ፤ ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ይጎድል ነበር፤ በአሥረኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ራሶች ተገለጡ።
6 ፤ ከአርባ ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፥
7 ፤ ቁራንም ሰደደው፤ እርሱም ወጣ፤ ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር።
8 ፤ ርግብንም ውኃው ከምድር ፊት ቀልሎ እንደ ሆነ እንድታይ ከእርሱ ዘንድ ሰደዳት።
9 ፤ ነገር ግን ርግብ እግርዋን የምታሳርፍበት ስፍራ አላገኘችም፥ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ተመለሰች፥ ውኃ በምድር ላይ ሁሉ ስለ ነበረ፤ እጁን ዘረጋና ተቀበላት፥ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ውስጥ አገባት።
10 ፤ ከዚያም በኋላ ደግሞ እስከ ሰባት ቀን ቆየ፤ ርግብንም እንደ ገና ከመርከብ ሰደደ።
11 ፤ ርግብም በማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች፤ በአፍዋም እነሆ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖኅም ከምድር ላይ ውኃ እንደ ቀለለ አወቀ።
12 ፤ ደግሞ እስከ ሰባት ቀን ቆየ፤ ርግብንም ሰደዳት ዳግመኛም ወደ እርሱ አልተመለሰችም።
13 ፤ በኖኅ ዕድሜ በስድስት መቶ አንድ ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውኃው ከምድር ላይ ደረቀ፤ ኖኅም የመርከቢቱን ክዳን አነሣ፥ እነሆም፥ ውኃው ከምድር ፊት እንደ ደረቀ አየ።
14 ፤ በሁለተኛውም ወር ከወሩም በሀያ ሰባተኛው ቀን ምድር ደረቀች።
15 ፤ እግዚአብሔርም ለኖኅ እንዲህ ብሎ ነገረው።
16 ፤ አንተ ሚስትህንና ልጆችህን የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ከመርከብ ውጣ።
17 ፤ ከአንተ ጋር ያሉትን አራዊት ሁሉ፥ ሥጋ ያላቸውን ሁሉ፥ ወፎችንና እንስሶችን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ከአንተ ጋር አውጣቸው፤ በምድር ላይ ይርመስመሱ፥ ይዋለዱ፥ በምድርም ላይ ይብዙ።
18 ፤ ኖኅም ልጆቹንና ሚስቱን የልጆቹንም ሚስቶች ይዞ ወጣ፤
19 ፤ አራዊት ሁሉ፥ ተንቀሳቃሾች ሁሉ፥ ወፎችም ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚርመሰምሰው ሁሉ በየዘመዳቸው ከመርከብ ወጡ።
20 ፤ ኖኅም ለእግዚአብሔር መሠውያውን ሠራ፥ ከንጹሕም እንስሳ ሁሉ ከንጹሐን ወፎችም ሁሉ ወሰደ፥ በመሠውያውም ላይ መሥዋዕትን አቀረበ።
21 ፤ እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ፤ እግዚአብሔርም በልቡ አለ። ምድርን ዳግመኛ ስለ ሰው አልረግምም፥ የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና፤ ደግሞም ከዚህ ቀድሞ እንዳደረግሁት ሕያዋንን ሁሉ እንደ ገና አልመታም።
22 ፤ በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም።