ምዕራፍ 25

አብርሃምም ደግሞ ስምዋ ኬጡራ የተባላች ሚስት አገባ።
2 ፤ እርስዋም ዘምራንን፥ ዮቅሳንን፥ ሜዳንን፥ ምድያምን፥ የስቦቅን፥ ስዌሕን ወለደችለት።
3 ፤ ዮቅሳንም ሳባንና ድዳንን ወለደ። የድዳንም ልጆች አሦርያውያን፥ ለጡሳውያን፥ ለኡማውያን ናቸው።
4 ፤ የምድያምም ልጆች ጌፌር፥ ዔፌር፥ ሄኖኅ፥ አቢዳዕ፥ ኤልዳዓ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው።
5 ፤ አብርሃምም የነበረውን ሁሉ ለይስሐቅ ሰጠው፤
6 ፤ የአብርሃምም ለነበሩ ለቁባቶቹ ልጆች አብርሃም ስጦታን ሰጣቸው፤ እርሱም ገና በሕይወቱ ሳለ ከልጁ ከይስሐቅ ለይቶ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደ ምሥራቅ አገር ሰደዳቸው።
7 ፤ አብርሃምም የኖረበት የዕድሜው ዓመታት እነዚህ ናቸው፤ መቶ ሰባ አምስት ዓመት ኖረ።
8 ፤ አብርሃምም ነፍሱን ሰጠ፥ በመልካም ሽምግልናም ሞተ፤ ሸመገለም፥ ብዙ ዘመንም ጠገበ፤ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ።
9 ፤ ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤልም በመምሬ ፊት ለፊት ባለው በኬጢያዊ በሰዓር ልጅ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ ቀበሩት ።
10 ፤ አብርሃም ከኬጢ ልጆች የገዛው እርሻ ይህ ነው፤ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ከዚያ ተቀበሩ።
11 ፤ አብርሃምም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር ልጁን ይስሐቅን ባረከው፤ ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ በሚጠራው ምንጭ አጠገብ ኖረ።
12 ፤ የሣራ ባሪያ ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችው የአብርሃም ልጅ የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው፤
13 ፤ የእስማኤልም የልጆቹ ስም በየስማቸውና በየትውልዳቸው እንዲህ ነው፤ የእስማኤል የበኵር ልጁ
14 ፤ ነባዮት፥ ቄዳር፥ ነብዳኤል፥ መብሳም፥ ማስማዕ፥
15 ፤ ዱማ፥ ማሣ፥ ኩዳን፥ ቴማን፥ ኢጡር፥ ናፌስ፥ ቄድማ።
16 ፤ የእስማኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ስማቸውም በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው ይኸው ነው፤ በየወገናቸውም አሥራ ሁለት አለቆች ናቸው።
17 ፤ እስማኤልም የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው፤ ነፍሱን ሰጠ ሞተም፤ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ።
18 ፤ መኖሪያቸውም ከኤውላጥ አንሥቶ በግብፅ ፊት ለፊት እስከምትገኝ እስከ ሱር ድረስ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ ላይ ነበረ፤ እንዲህም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ተቀመጠ።
19 ፤ የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድም ይህ ነው፤ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤
20 ፤ ይስሐቅም አርባ ዓመት ሲሆነው ርብቃን አገባ፤ እርስዋም በሁለት ወንዞች መካከል ያለ የሶርያዊው የባቱኤል ልጅና የሶርያዊው የላባ እኅት ናት።
21 ፤ ይስሐቅም ስለሚስቱ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ መካን ነበረችና፤ እግዚአብሔርም ተለመነው፥ ርብቃም ሚስቱ ፀነሰች።
22 ፤ ልጆችም በሆድዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤ እርስዋም። እንዲህ ከሆነ ይህ ለእኔ ምኔ ነው? አለች። ከእግዚአብሔርም ትጠይቅ ዘንድ ሄደች።
23 ፤ እግዚአብሔርም አላት። ሁለት ወገኖች በማኅፀንሽ ናቸው፥ ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል።
24 ፤ ትወልድ ዘንድ ዘመንዋ በተፈጸመ ጊዜም፥ እነሆ፥ በማኅፀንዋ መንታ ነበሩ።
25 ፤ በፊትም የወጣው ቀይ ነበረ፥ ሁለንተናውም ጠጕር ለብሶ ነበር፤ ስሙም ዔሳው ተባለ።
26 ፤ ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ፥ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስሙም ያዕቆብ ተባለ። እርስዋ ልጆችን በወለደቻቸው ጊዜ ይስሐቅ ስድሳ ዓመት ሆኖት ነበር።
27 ፤ ብላቴኖቹም አደጉ፤ ዔሳውም አደን የሚያውቅ የበረሃ ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፥ በድንኳንም ይቀመጥ ነበር።
28 ፤ ይስሐቅም ዔሳውን ይወድ ነበር፥ ካደነው ይበላ ነበርና፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበረች።
29 ፤ ያዕቆብም ወጥ ሠራ፤ ዔሳውም ደክሞ ከበረሃ ገባ፤
30 ፤ ዔሳውም ያዕቆብን። ከዚህ ከቀዩ ወጥ አብላኝ፥ እኔ እጅግ ደክሜአለሁና አለው፤ ስለዚህ ስሙ ኤዶም ተባለ።
31 ፤ ያዕቆብም። በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ አለው።
32 ፤ ዔሳውም። እነሆ፥ እኔ ልሞት ነኝ፤ ይህች ብኵርና ለምኔ ናት? አለ ።
33 ፤ ያዕቆብም። እስኪ በመጀመሪያ ማልልኝ አለው። ማለለትም፤ ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠ።
34 ፤ ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ በላ፥ ጠጣ፥ ተነሥቶም ሄደ፤ እንዲሁም ዔሳው ብኵርናውን አቃለላት።