ምዕራፍ 46

እስራኤልም ለእርሱ ያለውን ሁሉ ይዞ ተነሣ፥ ወደ ቤርሳቤህ መጣ፥ መሥዋዕትንም ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ ሠዋ።
2 ፤ እግዚአብሔርም በሌሊት ራእይ። ያዕቆብ ያዕቆብ ብሎ ለእስራኤል ተናገረው። እርሱም። እነሆኝ አለ።
3 ፤ አለውም። የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ወደ ግብፅ መውረድ አትፍራ፥ በዚያ ትልቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና።
4 ፤ እኔ ወደ ግብፅ አብሬህ እወርዳለሁ፥ ከዚያም ደግሞ እኔ አወጣሃለሁ፤ ዮሴፍም እጁን በዓይንህ ላይ ያኖራል።
5 ፤ ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ተነሣ፤ የእስራኤልም ልጆች ያዕቆብን ይወስዱ ዘንድ ፈርዖን በሰደዳቸው ሰረገሎች አባታቸውን ያዕቆብንና ሕፃናቶቻቸውን ሴቶቻቸውንም ወሰዱ።
6 ፤ እንስሶቻቸውንም በከነዓን አገርም ያገኙትን ከብታቸውን ሁሉ ይዘው ያዕቆብና ዘሩ ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ መጡ፤
7 ፤ ወንዶች ልጆቹንና የልጆቹን ወንዶች ልጆች፥ ሴቶች ልጆቹንና የወንዶች ልጆቹን ሴቶች ልጆች፥ ዘሩንም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ አስገባቸው።
8 ፤ ወደ ግብፅም የገቡት የእስራኤል ልጆች ስም ይህ ነው፥ ያዕቆብና ልጆቹ፤ የያዕቆብ በኵር ሮቤል።
9 ፤ የሮቤልም ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉሶ፥ አስሮን፥ ከርሚ።
10 ፤ የስሞዖን ልጆች፤ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ጾሐር፥ የከነዓናዊት ልጅ ሳኡል።
11 ፤ የሌዊም ልጆች፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ።
12 ፤ የይሁዳም ልጆች፤ ዔር፥ አውናን፥ ሴሎም፥ ፋሬስ፥ ዛራ፤ ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ፤ የፋሬስም ልጆች ኤስሮም፥ ሐሙል።
13 ፤ የይሳኮርም ልጆች፤ ቶላ፥ ፉዋ፥ ዮብ፥ ሺምሮን።
14 ፤ የዛብሎንም ልጆች፤ ሴሬድ፥ ኤሎን፥ ያሕልኤል።
15 ፤ ልያ በመስጴጦምያ በሶርያ ለያዕቆብ የወለደቻቸው ልጆችና ሴቲቱ ልጅዋ ዲና እነዚህ ናቸው፤ ወንዶችም ሴቶችም ልጆችዋ ሁሉ ሠላሳ ሦስት ነፍስ ናቸው።
16 ፤ የጋድም ልጆች ጽፎን፥ ሐጊ፥ ሹኒ፥ ኤስቦን፥ ዔሪ፥ አሮዲ፥ አርኤሊ።
17 ፤ የአሴርም ልጆች፤ ዪምና፥ የሱዋ፥ የሱዊ፥ በሪዓ፥ እኅታቸው ሤራሕ፤ የበሪዓ ልጆችም፤ ሔቤር፥ መልኪኤል።
18 ፤ ላባ ለልጁ ለልያ የሰጣት የዘለፋ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህን አሥራ ስድስቱንም ነፍስ ለያዕቆብ ወለደች።
19 ፤ የያዕቆብ ሚስት የራሔል ልጆች ዮሴፍና ብንያም ናቸው።
20 ፤ ለዮሴፍም በግብፅ ምድር ምናሴና ኤፍሬም ተወለዱለት፤ የሄልዮቱ ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት የወለደቻቸው ናቸው።
21 ፤ የብንያምም ልጆች፤ ቤላ፥ ቤኬር፥ አስቤል፤ የቤላ ልጆችም፤ ጌራ፥ ናዕማን፥ አኪ፥ ሮስ፥ ማንፌን፥ ሑፊም፤ ጌራም አርድን ወለደ።
22 ፤ ለያዕቆብ የተወለዱለት የራሔልም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሁሉም አሥራ አራት ነፍስ ናቸው።
23 ፤ የዳንም ልጆች፤ ሑሺም።
24 ፤ የንፍታሌምም ልጆች፤ ያሕጽኤል፥ ጉኒ፥ ዬጽር፥ ሺሌም።
25 ፤ ላባ ለልጁ ለራሔል የሰጣት የባላ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህንም ለያዕቆብ ወለደችለት፤ ሁሉም ሰባት ነፍስ ናቸው።
26 ፤ ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት ሰዎች ሁሉ ከጉልበቱ የወጡት፥ ከልጆቹ ሚስቶች ሌላ፥ ሁላቸው ስድሳ ስድስት ናቸው።
27 ፤ በግብፅ ምድር የተወለዱለት የዮሴፍም ልጆች ሁለት ናቸው፤ ወደ ግብፅ የገቡት የያዕቆብ ቤተ ሰዎች ሁሉ ሰባ ናቸው።
28 ፤ ይሁዳንም በጌሤም እንዲቀበለው በፊቱ ወደ ዮሴፍ ላከ፤ ወደ ጌሤም ምድርም ደረሱ።
29 ፤ ዮሴፍም ሰረገላውን አዘጋጀ፥ አባቱንም እስራኤልን ሊገናኘው ወደ ጌሤም ወጣ፤ ባየውም ጊዜ በአንገቱ ላይ ወደቀ፥ አቅፎትም ረጅም ጊዜ አለቀሰ።
30 ፤ እስራኤልም ዮሴፍን። አንተ ገና በሕይወት ሳለህ ፊትህን አይቼአለሁና አሁን ልሙት አለው።
31 ፤ ዮሴፍም ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው። እኔ መጥቼ ለፈርዖን እንዲህ ብዬ እነግረዋለሁ። በከነዓን ምድር የነበሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤተ ሰዎች ወደ እኔ መጥተዋል፤
32 ፤ እነርሱም በግ የሚጠብቁ ሰዎች ናቸው፥ እንስሳ ያረቡ ነበርና፤ በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ያላቸውንም ሁሉ አመጡ።
33 ፤ ፈርዖንም ቢጠራችሁ። ተግባራችሁስ ምንድር ነው? ቢላችሁ፥
34 ፤ በግ ጠባቂ ሁሉ ለግብፅ ሰዎች ርኵስ ነውና በጌሤም እንድትቀመጡ እንዲህ በሉት። እኛ ባሪያዎችህ ከብላቴናነታችን ጀምረን እስከ አሁን ድረስ፥ እኛም አባቶቻችንም፥ እንስሳ አርቢዎች ነን። q ቍ@
28 ፤ ጌሤም የሚለውን የግእዝ መጽሐፍ ራምሴ ይለዋል።