ምዕራፍ 24

እነሆ፥ እግዚአብሔር ምድርን ባዶ ያደርጋታል፥ ባድማም ያደርጋታል፥ ይገለብጣትማል፥ በእርስዋም የተቀመጡትን ይበትናል።
2 ፤ እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ፥ እንደ ባሪያውም እንዲሁ ጌታው፥ እንደ ባሪያይቱም እንዲሁ እመቤትዋ፥ እንደሚገዛም እንዲሁ የሚሸጠው፥ እንደ አበዳሪውም እንዲሁ ተበዳሪው፥ እንደ ዕዳ አስከፋዩም እንዲሁ ዕዳ ከፋዩ ይሆናል።
3 ፤ ምድር መፈታትን ትፈታለች፥ ፈጽማም ትበላሻላች፤ እግዚአብሔር ይህን ቃል ተናግሮአልና።
4 ፤ ምድርም አለቀሰች ረገፈችም፤ ዓለም ደከመች ረገፈችም፤ የምድርም ሕዝብ ታላላቆች ደከሙ።
5 ፤ ምድርም ከሚቀመጡባት በታች ረክሳለች፥ ሕጉን ተላልፈዋልና፥ ሥርዓቱንም ለውጠዋልና፥ የዘላለሙንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና።
6 ፤ ስለዚህ መርገም ምድርን ትበላለች በእርስዋም የተቀመጡ ይቀጣሉ፤ ስለዚህ የምድር ሰዎች ይቃጠላሉ ጥቂት ሰዎችም ይቀራሉ።
7 ፤ የወይን ጠጅ አለቀሰች፥ የወይን ንግድ ደከመች፥ ልባቸው ደስ ያለው ሁሉ ተከዙ።
8 ፤ የከበሮው ሐሤት ቀርቶአል፥ የደስተኞች ድምፅ ዝም ብሎአል፥ የመሰንቆ ደስታ ቀርቶአል።
9 ፤ እየዘፈኑም የወይን ጠጅን አይጠጡትም፥ የሚያሰክርም መጠጥ ለሚጠጡት መራራ ይሆናል።
10 ፤ ባድማ የሆነችው ከተማ ፈረሰች፤ ቤት ሁሉ ማንም እንዳይገባበት ተዘጋ።
11 ፤ ስለ ወይኑም ጠጅ በአደባባይ ጩኸት ይሆናል፤ ደስታ ሁሉ ጨልሞአል፥ የምድርም ሐሤት ፈርሶአል።
12 ፤ ከተማይቱም ባድማ ሆናለች፥ በርዋም በጥፋት ተመትቶአል።
13 ፤ የወይራን ዛፍ እንደ መምታት፥ ከወይንም መከር በኋላ ቃርሚያውን እንደ መልቀም፥ እንዲሁ በምድር መካከል በአሕዛብም መካከል ይሆናል።
14 ፤ እነዚህ ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ እልልም ይላሉ፥ ስለ እግዚአብሔር ክብርም ከባሕር ይጣራሉ።
15 ፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን በምሥራቅ፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርንም ስም በባሕር ደሴቶች አክብሩ።
16 ፤ ለጻድቁ ክብር ይሁን የሚለውን ዝማሬ ከምድር ዳርቻ ሰምተናል። እኔ ግን። ከሳሁ፥ ከሳሁ፥ ወዮልኝ! ወንጀለኞች ወንጅለዋል፤ ወንጀለኞች እጅግ ወንጅለዋል አልሁ።
17 ፤ በምድር ላይ የምትኖር ሆይ፥ ፍርሃትና ገደል ወጥመድም በአንተ ላይ አሉ።
18 ፤ የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፥ የምድርም መሠረት ተናውጣለችና ከፍርሃት ድምፅ የሸሸ በገደል ይወድቃል፥ ከገደልም የወጣ በወጥመድ ይያዛል።
19 ፤ ምድር ተሰባበረች፥ ምድር ፈጽማ ደቀቀች፥ ምድር ተነዋወጠች።
20 ፤ ምድር እንደ ሰካር ሰው ትንገዳገዳለች፥ እንደ ዳስም ትወዛወዛለች፤ መተላለፍዋ ይከብድባታል፥ ትወድቅማለች ደግማም አትነሣም።
21 ፤ በዚያም ቀን እንደዚህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር በከፍታ ያለውን ሠራዊት በከፍታ ላይ፥ በምድርም ያሉትን ነገሥታት በምድር ላይ ይቀጣቸዋል።
22 ፤ ግዞተኞች በጕድጓድ እንደሚከማቹ በአንድነት ይከማቻሉ፥ በግዞት ቤትም ውስጥ ተዘግተው ይኖራሉ፥ ከብዙ ቀንም በኋላ ይጐበኛሉ።
23 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ ይነግሣልና፥ በሽማግሌዎቹም ፊት ክብር ይሆናልና ጨረቃ ይታወካል ፀሐይም ያፍራል።