ምዕራፍ 6

ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር።
2 ፤ ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር።
3 ፤ አንዱም ለአንዱ። ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር።
4 ፤ የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፥ ቤቱንም ጢስ ሞላበት።
5 ፤ እኔም። ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፥ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ! አልሁ።
6 ፤ ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጕጠት የወሰደው ፍም ነበረ።
7 ፤ አፌንም ዳሰሰበትና። እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረየልህ አለኝ።
8 ፤ የጌታንም ድምፅ። ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም። እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ።
9 ፤ እርሱም። ሂድ፥ ይህን ሕዝብ። መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው።
10 ፤ በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፥ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፥ ጆሮአቸውንም አደንቍር፥ ዓይናቸውንም ጨፍን አለኝ።
11 ፤ እኔም። ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው? አልሁ። እርሱም መልሶ እንዲህ አለ። ከተሞች የሚኖርባቸውን አጥተው እስኪፈርሱ ድረስ፥ ቤቶችም ሰው አልቦ እስኪሆኑ ምድርም ፈጽሞ ባድማ ሆና እስክትቀር ድረስ፥
12 ፤ እግዚአብሔርም ሰዎችን እስኪያርቅ፥ በምድርም መካከል ውድማው መሬት እስኪበዛ ድረስ ነው።
13 ፤ በእርስዋም ዘንድ አሥረኛ እጅ ቀርቶ እንደ ሆነ እርሱ ደግሞ ይቃጠላል፤ በተቈረጡ ጊዜ ጉቶቻቸው እንደ ቀሩ እንደ ግራርና እንደ ኮምበል ዛፍ ሆኖ፥ ጉቶው የተቀደሰ ዘር ይሆናል።