ምዕራፍ 53

የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል?
2 ፤ በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም።
3 ፤ የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም።
4 ፤ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው።
5 ፤ እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።
6 ፤ እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።
7 ፤ ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።
8 ፤ በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ?
9 ፤ ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገንበትም ነበር።
10 ፤ እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈከደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል።
11 ፤ ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሰከማል።
12 ፤ ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።