ምዕራፍ 35

ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፥ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል።
2 ፤ እጅግ ያብባል በደስታና በዝማሬ ሐሤትን ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር፥ የቀርሜሎስና የሳሮን ግርማ ይሰጠዋል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።
3 ፤ የደከሙትን እጆች አበርቱ፥ የላሉትንም ጕልበቶች አጽኑ።
4 ፤ ፈሪ ልብ ላላቸው። እነሆ፥ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፥ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፥ አትፍሩ በሉአቸው።
5 ፤ በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል፤ የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል።
6 ፤ በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፥ የድዳም ምላስ ይዘምራል፤ በምድረ በዳ ውኃ፥ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና።
7 ፤ ደረቂቱ ምድር ኵሬ፥ የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች፤ ቀበሮ የተኛበት መኖሪያ ልምላሜና ሸምበቆ ደንገልም ይሆንበታል።
8 ፤ በዚያም ጐዳናና መንገድ ይሆናል እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፤ ንጹሐንም ያልሆኑ አያልፉበትም፥ ለንጹሐን ግን ይሆናል፤ ተላላፊዎችና ሰነፎች እንኳ አይስቱበትም።
9 ፤ አንበሳም አይኖርበትም፥ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፥ ከዚያም አይገኙም፤ የዳኑት ግን በዚያ ይሄዳሉ፤
10 ፤ እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።