ምዕራፍ 63

ይህ ከኤዶምያስ፥ ልብሱም የቀላ ከባሶራ የሚመጣ፥ አለባበሱ ያማረ፥ በጕልበቱ ጽናት የሚራመድ ማን ነው? በጽድቅ የምናገር ለማዳንም የምበረታ እኔ ነኝ።
2 ፤ ቀሚስህ ስለ ምን ቀላ? ልብስህስ በወይን መጥመቂያ እንደሚረግጥ ሰው ልብስ ስለ ምን መሰለ?
3 ፤ መጥመቂያውን ብቻዬን ረግጫለሁ፥ ከአሕዛብም አንድ ሰው ከእኔ ጋር አልነበረም፤ በቍጣዬ ረገጥኋቸው በመዓቴም ቀጠቀጥኋቸው፤ ደማቸውም በልብሴ ላይ ተረጭቶአል፥ ልብሴንም ሁሉ አስድፌአለሁ።
4 ፤ የምበቀልበት ቀን በልቤ ነውና፥ የምቤዥበትም ዓመት ደርሶአልና።
5 ፤ ተመለከትሁ፥ የሚረዳም አልተገኘም፤ የሚያግዝም አልነበረምና ተደነቅሁ፤ ስለዚህ የገዛ ክንዴ መድኃኒት አመጣልኝ፥ ቍጣዬም እርሱ አገዘኝ።
6 ፤ በቍጣዬም አሕዛብን ረገጥሁ በመዓቴም ቀጠቀጥኋቸው፥ ደማቸውንም ወደ ምድር አፈሰስሁት።
7 ፤ እግዚአብሔር እንደ ሰጠን ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቸርነትና የእግዚአብሔርን ምስጋና፥ እንደ ምሕረቱና እንደ ቸርነቱም ብዛት ለእስራኤል ቤት የሰጠውን ትልቅ በጎነት አሳስባለሁ።
8 ፤ እርሱም። በእውነት ሕዝቤ፥ ሐሰትን የማያደርጉ ልጆች፥ ናቸው አለ፤ መድኃኒትም ሆነላቸው።
9 ፤ በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው።
10 ፤ እነርሱ ግን ዐመፁ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፤ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፥ እርሱም ተዋጋቸው።
11 ፤ እርሱም እንዲህ ብሎ የቀደመውን ዘመን አሰበ። የበጎቹን እረኛ ከባሕሩ ያወጣው ወዴት ነው ያለ? ቅዱስ መንፈሱንም በመካከላቸው ያኖረ ወዴት ነው ያለ?
12 ፤ የከበረውንም ክንድ በሙሴ ቀኝ ያስሄደ፥ ለራሱም የዘላለምን ስም ያደርግ ዘንድ ውኃውን በፊታቸው የከፈለ፥
13 ፤ በምድረ በዳም እንደሚያልፍ ፈረስ፥ በቀላይ ውስጥ ያለ ዕንቅፋት ያሳለፋቸው ወዴት ነው ያለ?
14 ፤ ወደ ሸለቆ እንደሚወርዱ ከብቶች፥ እንዲሁ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ዕረፍት አመጣቸው፤ እንዲሁም ለራስህ የከበረ ስም ታደርግ ዘንድ ሕዝብን መራህ።
15 ፤ ከሰማይ ተመልከት፥ ከቅዱስነትህና ከክብርህም ማደሪያ ጐብኝ፤ ቅንዓትህና ኃይልህስ ወዴት ነው? ለእኔም የሆነው የልብህ ናፍቆትና ርኅራኄህ ተከለከለ።
16 ፤ አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ፤ አቤቱ፥ አንተ አባታችን ነህ፥ ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው።
17 ፤ አቤቱ፥ ከመንገድህ ለምን አሳትኸን? እንዳንፈራህም ልባችንን ለምን አጸናህብን? ስለ ባሪያዎችህ ስለ ርስትህ ነገዶች ተመለስ።
18 ፤ የተቀደሰው ሕዝብህ መቅደስህን ጥቂት ጊዜ ወረሱት፤ ጠላቶቻችንም ረግጠውታል።
19 ፤ ከዘላለም እንዳልገዛኸን በስምህም እንዳልተጠራን ሆነናል።