ምዕራፍ 26

በዚያም ቀን ይህ ቅኔ በይሁዳ ምድር ይዘመራል። የጸናች ከተማ አለችን፤ ለቅጥርና ለምሽግ መድኃኒትን ያኖርባታል።
2 ፤ እውነትን የሚጠብቅ ጻድቅ ሕዝብ ይገባ ዘንድ በሮችን ክፈቱ።
3 ፤ በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።
4 ፤ ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አምባ ነውና ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ።
5 ፤ በከፍታ የሚኖሩትን ሰዎች ዝቅ ያደርጋል፤ ከፍ ያለችውን ከተማ ያዋርዳል፥ እስከ መሬትም ድረስ ያዋርዳታል፥ እስከ አፈርም ድረስ ይጥላታል።
6 ፤ እግር፥ የድሀ እግርም የችግረኛም አረጋገጥ፥ ትረግጣታለች።
7 ፤ የጻድቃን መንገድ ቅን ናት፤ አንተ ቅን የሆንህ የጻድቃንን መንገድ ታቃናለህ።
8 ፤ አቤቱ፥ በፍርድህ መንገድ ተስፋ አድርገንሃል፥ ስምህም መታሰቢያህም የነፍሳችን ምኞት ነው።
9 ፤ ፍርድህን በምድር ባደረግህ ጊዜ በዓለም የሚኖሩት ጽድቅን ይማራሉና ነፍሴ በሌሊት ትናፍቅሃለች፥ መንፈሴም በውስጤ ወደ አንተ ትገሠግሣለች።
10 ፤ ለኃጢአተኛ ሞገስ ቢደረግለት ጽድቅን አይማርም፤ በቅኖች ምድር ክፉን ነገር ያደርጋል፥ የእግዚአብሔርንም ግርማ አያይም።
11 ፤ አቤቱ፥ እጅህ ከፍ ከፍ አለች አላዩምም፤ ነገር ግን በሕዝብህ ላይ ያለህን ቅንዓት አይተው ያፍራሉ፤ እሳትም ጠላቶችህን ትበላለች።
12 ፤ አቤቱ፥ ሥራችንን ሁሉ ሠርተህልናልና ሰላምን ትሰጠናለህ።
13 ፤ አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ ከአንተ በቀር ሌሎች ጌቶች ገዝተውናል፤ ነገር ግን በአንተ ብቻ ስምህን እናስባለን።
14 ፤ እነርሱ ሞተዋል፥ በሕይወት አይኖሩም፤ ጠፍተዋል፥ አይነሡም፤ ስለዚህ አንተ ጐብኝተሃቸዋል አጥፍተሃቸውማል፥ መታሰቢያቸውንም ሁሉ ምንምን አድርገሃል።
15 ፤ ሕዝብን አበዛህ፥ አቤቱ፥ ሕዝብን አበዛህ፤ አንተም ተከበርህ፥ የአገሪቱንም ዳርቻ ሁሉ አሰፋህ።
16 ፤ አቤቱ፥ በመከራ ጊዜ ፈለጉህ፥ በገሰጽሃቸውም ጊዜ ልመናቸውን ወደ አንተ አፈሰሱ።
17 ፤ የፀነሰች ሴት ለመውለድ ስትቀርብ እንደምትጨነቅና በምጥ እንደምትጮኽ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ በፊትህ ሆነናል።
18 ፤ እኛ ፀንሰናል ምጥም ይዞናል፥ ነፋስንም እንደምንወልድ ሆነናል፤ በምድርም ደኅንነት አላደረግነም፤ በዓለምም የሚኖሩ ይወድቃሉ።
19 ፤ ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ። በምድር የምትኖሩ ሆይ፥ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፥ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም።
20 ፤ ሕዝቤ ሆይ፥ ና ወደ ቤትህም ግባ፥ ደጅህን በኋላህ ዝጋ ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።
21 ፤ በምድር በሚኖሩት ላይ በበደላቸው ምክንያት ቍጣውን ያመጣባቸው ዘንድ፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፤ ምድርም ደምዋን ትገልጣለች፥ ሙታኖችዋንም ከእንግዲህ ወዲህ አትከድንም።