ምዕራፍ 52

ጽዮን ሆይ፥ ተነሺ፥ ተነሺ፥ ኃይልሽን ልበሺ፤ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ያልተገረዘና ርኩስ ከእንግዲህ ወዲህ አይገባብሽምና ጌጠኛ ልብስሽን ልበሺ።
2 ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ትቢያን አራግፊ፤ ተነሺ፥ ተቀመጪ፤ ምርኮኛይቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ የአንገትሽን እስራት ፍቺ።
3 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በከንቱ ተሽጣችሁ ነበር፥ ያለ ገንዘብም ትቤዣላችሁ።
4 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወገኔ በዚያ እንግዳ ሆኖ ይቀመጥ ዘንድ አስቀድሞ ወደ ግብጽ ወረደ፥ አሦርም ያለ ምክንያት በደለው።
5 ፤ ወገኔ በከንቱ ተወስዶአልና አሁን ከዚህ ምን አለኝ? ይላል እግዚአብሔር፤ የሚገዙአቸው ይጮኻሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ስሜም ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ይሰደባል።
6 ፤ ስለዚህ ወገኔ ስሜን ያውቃል፥ ስለዚህም የምናገር እኔ እንደ ሆንሁ በዚያ ቀን ያውቃሉ፤ እነሆ፥ እኔ ነኝ።
7 ፤ የምስራች የሚናገር፥ ሰላምንም የሚያወራ፥ የመልካምንም ወሬ የምስራች የሚናገር፥ መድኃኒትንም የሚያወራ፥ ጽዮንንም። አምላክሽ ነግሦአል የሚል ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው።
8 ፤ እነሆ፥ ጕበኞችሽ ጮኸዋል፤ እግዚአብሔር ወደ ጽዮን በተመለሰ ጊዜ ዓይን በዓይን ይተያያሉና ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ በአንድነትም ይዘምራሉ።
9 ፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች ሆይ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአልና፥ ኢየሩሳሌምንም ታድጎአልና ደስ ይበላችሁ፥ በአንድነትም ዘምሩ።
10 ፤ እግዚአብሔር የተቀደሰውን ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ገልጦአል፥ በምድር ዳርቻ የሚኖሩትም ሁሉ የአምላካችንን መድኃኒት ያያሉ።
11 ፤ እናንተ የእግዚአብሔር ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፥ እልፍ በሉ፥ እልፍ በሉ፥ ከዚያ ውጡ፥ ርኩስን ነገር አትንኩ፥ ከመካከልዋ ውጡ፥ ንጽሐን ሁኑ።
12 ፤ እግዚአብሔር ይቀድማችኋልና፥ የእስራኤልም አምላክ ይከተላችኋልና በችኰላ አትወጡም በመኰብለልም አትሄዱም።
13 ፤ እነሆ፥ ባሪያዬ በማስተዋል ያደርጋል፤ ይከብራል ከፍ ከፍም ይላል፥ እጅግ ታላቅም ይሆናል።
14 ፤ ፊቱ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ፥ መልኩም ከሰዎች ልጆች ይልቅ ተጐሳቍሎአልና ብዙ ሰዎች ስለ አንተ እንደ ተደነቁ፥ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን ያስደንቃል፤
15 ፤ ያልተነገረላቸውንም ያያሉና፥ ያልሰሙትንም ያስተውላሉና ነገሥታት ስለ እርሱ አፋቸውን ይዘጋሉ።